ሴኔጋል ያሸነፈችው የአፍሪካ ዋንጫ ተነጥቆ ለሞሮኮ ተሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
ሴኔጋል ያሸነፈችው የአፍሪካ ዋንጫ ተነጥቆ ለሞሮኮ ተሰጠ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 9/2018 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን (ካፍ) የ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የፍጻሜ ውጤት ተሽሮ ዋንጫው ለሞሮኮ እንዲሰጥ መወሰኑን አስታወቀ።
ውሳኔው ከፍተኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል።
አህጉራዊው የእግር ኳስ የበላይ አካል ከውሳኔው ላይ የደረሰው የፍጻሜውን ጨዋታ ውጤት ላይ ምርመራ ካደረገ በኋላ መሆኑን የካፍ የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት አስታውቋል።
ሞሮኮ ባስተናገደችው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በፍጻሜው ጨዋታ 1 ለ 0 ተሸንፋ ሴኔጋል ዋንጫውን ማንሳቷ የሚታወስ ነው።
በፍጻሜው ጨዋታ ለሞሮኮ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት በመቃወም የሴኔጋል ተጫዋቾች ለ15 ደቂቃ ያህል ሜዳ ጥለው መውጣታቸው የውድድሩን ህግ አንቀጽ 84 (Article 84) የሚጥስ ሆኖ መገኘቱን ካፍ ገልጿል።
የሞሮኮ እግር ኳስ ፌዴሬሽን (FRMF) ያቀረበውን ይግባኝ ለመመርመር የተሰበሰበው የካፍ የይግባኝ ሰሚ ቦርድ የዲሲፕሊን ኮሚቴው ቀደም ብሎ ያስተላለፈውን ውሳኔ በመሻር ዋንጫውን ከሴኔጋል ተነጥቆ ለሞሮኮ እንዲሰጥ ወስኗል።
በዚሁ መሰረት ቦርዱ የ1 ለ 0 ውጤቱን በመሻር ሞሮኮ የ3 ለ 0 የፎርፌ ውጤት እንድታገኝ መደረጉን አመልክቷል።
ይህ ውሳኔ ሞሮኮ ከ50 ዓመታት በኋላ የአፍሪካ ዋንጫን ለሁለተኛ ጊዜ እንድታነሳ አስችሏታል።
ሴኔጋል ለሁለተኛ ጊዜ ያነሳችው የአፍሪካ ዋንጫ ተነጥቃለች።
ካፍ ያስተላለፈው ውሳኔ አስገራሚ፣ ታሪካዊ፣ ያልተጠበቀ እና አወዛጋቢ በሚል በእግር ኳስ አፍቃሪን ዘንድ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኗል።
የሴኔጋል እግር ኳስ ፌዴሬሽን በበኩሉ ባወጣው መግለጫ፤ ካፍ ያሳለፈውን ውሳኔ ኢ-ፍትሐዊ እና ተቀባይነት የሌለው ሲል ገልጾታል።
ውሳኔው የአፍሪካን እግር ኳስ ገጽታ ያበላሸ ነውም ብሏል።
ፌዴሬሽኑ ውሳኔው እንዲታይ ወደ ዓለም አቀፍ የስፖርት ገላጋይ ፍርድ ቤት (CAS) እንደሚወስድ አመልክቷል።