የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 19ኛ ሳምንት ዛሬ ይጠናቀቃል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 19ኛ ሳምንት ዛሬ ይጠናቀቃል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 8/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 19ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።
ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ አዲስ አበባ ከተማ ከሲዳማ ቡና በአበበ በቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ።
አዲስ አበባ ከተማ በውድድር ዓመቱ ካከናወናቸው 18 ጨዋታዎች መካከል ያሸነፈው ሁለት ጊዜ ብቻ ነው። በ14ቱ ሲሸነፍ በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ ላይ ዘጠኝ ግቦችን ሲያስቆጥር 39 ጎሎችን አስተናግዷል።
ቡድኑ በስምንት ነጥብ የመጨረሻውን 14ኛ ደረጃን ይዟል።
በሊጉ ካደረጋቸው 18 ጨዋታዎች መካከል ሰባቱን ያሸነፈው ሲዳማ ቡና በበኩሉ ስምንት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በሶስት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። 17 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 23 ግቦች ተቆጥረውበታል።
ሲዳማ ቡና በ24 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
አዲስ አበባ ከተማ ባለፉት አራት የሊግ ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዷል። ሲዳማ ቡና በ18ኛ ሳምንት ሲዳማ ቡና ባህር ዳር ከተማን 1 ለ 0 አሸንፏል።
በተያያዘም ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ይርጋጨፌ ቡና ከመቻል በአበበ በቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ይርጋጨፌ ቡና በሊጉ 18 ጨዋታዎችን በማድረግ ሁለት ሲያሸንፍ በ11ዱ ተሸንፏል። አምስት ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። በጨዋታዎቹ ላይ ስምንት ግቦችን ሲያስቆጥር 26 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
አዲስ አዳጊው ይርጋጨፌ ቡና በ11 ነጥብ 11 ደረጃን ይዟል።
መቻል በውድድር ዓመቱ ካደረጋቸው 18 ጨዋታዎች በ11ዱ ድል ሲቀናው ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። በአምስት ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል። 32 ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ 10 ግቦችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ38 ነጥብ አራተኛ ላይ ተቀምጧል።
ይርጋጨፌ ቡና ባለፉት 10 የሊግ ጨዋታዎች አላሸነፈም። መቻል ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ድል ቀንቶታል።
ጨዋታው ይርጋጨፌ ቡና ወደ አሸናፊነት ለመመለስ፣ መቻል በድል ጉዞው ለመቀጠል የሚያደርጉት ነው።