ቀጥታ፡

ማንችስተር ዩናይትድ አስቶንቪላን በማሸነፍ ወሳኝ ሶስት ነጥብ አግኝቷል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 6/2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 30ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ማንችስተር ዩናይትድ አስቶንቪላ 3 ለ 1 አሸንፏል።


 

ማምሻውን በኦልድትራፎርድ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ካሲሚሮ፣ ማትያስ ኩንሃ እና ቤንጃሚን ሼስኮ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

ሮስ ባርክሌይ ለአስቶንቪላ ብቸኛውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።


 

በሊጉ 15ኛ ድሉን ያስመዘገበው ማንችስተር ዩናይትድ በ54 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።

ዩናይትድ በሻምፒዮንስ ሊግ ለመሳተፍ በሚያደርገው ፉክክር ወሳኝ ሶስት ነጥብ አግኝቷል።


 

በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ ዘጠነኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው አስቶንቪላ በ51 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። 

ቪላ ባለፉት አራት የሊግ ጨዋታዎች አላሸነፈም።

የማንችስተር ዩናይትዱ ብሩኖ ፈርናንዴዝ ዘንድሮ በሊጉ ለግብ አመቻችቶ ያቀበላቸውን ኳሶች ብዛት 16 አድርሷል። በዛሬው ጨዋታም በሁለት ግቦች ላይ ተሳትፎ ነበረው።


 

ይህም ዴቪድ ቤካም በዩናይትድ በአንድ የውድድር ዓመት 15 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን የማቀበል ክብረ ወሰን እንዲሰብር አድርጎታል።

በተመሳሳይ ሰዓት በተደረጉ የ30ኛ ጨዋታዎች ክሪስታል ፓላስ ከሊድስ ዩናይትድ፣ ኖቲንግሃም ፎረስት ከፉልሃም በተመሳሳይ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም