ስፖርቲንግ ሊዝበን የ3 ለ 0 ውጤት በመቀልበስ ለሩብ ፍጻሜ አለፈ - ኢዜአ አማርኛ
ስፖርቲንግ ሊዝበን የ3 ለ 0 ውጤት በመቀልበስ ለሩብ ፍጻሜ አለፈ
አዲስን አበባ፤ መጋቢት 8/2018 (ኢዜአ)፦ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ መርሃ ግብር ስፖርቲንግ ሊዝበን ቦዶ ግሊምትን 5 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፏል።
ማምሻውን በጆሴ አልቫላዴ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ጎንካሎ ኢናሲዮ እና ፖቴ በጨዋታ ሉዊስ ሱዋሬዝ በፍጹም ቅጣት ምት ሶስት ግቦችን አስቆጥረዋል።
ውጤቱን ተከትሎ ቡድኖቹ በድምር ውጤት ሶስት አቻ በመሆናቸው ጨዋታው ወደ ጭማሪ ሰዓት አምርቷል።
በጭማሪ ሰዓት ማክሲ አራውጆ በ92ኛው እና ራፋኤል ኔል በ121ኛው ደቂቃ ያስቆጠሯቸው ግቦች ስፖርቲንግን አሸናፊ አድርጓል።
የፖርቹጋሉ ክለብ የመጀመሪያ ዙር የ3 ለ 0 ውጤት ባልተጠበቀ ሁኔታ ቀልብሶ በድምር ውጤት 5 ለ 3 በማሸነፍ ሩብ ፍጻሜ የገባ የመጀመሪያ ክለብ ሆኗል።
ስፖርቲንግ ሊዝበን ሩብ ፍጻሜ ሲገባ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
በሩብ ፍጻሜው ከአርሰናል እና ባየር ሌቨርኩሰን አሸናፊ ጋር ይጫወታል።
ቦዶ ግሊምት ሩብ ፍጻሜ ለመጀመሪያ ጊዜ የመግባት ህልሙ አልተሳካም።
የቦዶ ግሊምት የሻምፒዮንስ ሊግ መልካም ግስጋሴ ጥሎ ማለፍ ላይ ተገቷል።
በአሁኑ ሰዓት ሪያል ማድሪድ ከማንችስተር ሲቲ፣ ቼልሲ ከፒኤስጂ እና አርሰናል ከባየር ሌቨርኩሰን ጨዋታቸውን እያደረጉ ይገኛል።
ጨዋታዎቹ ወደ ሩብ ፍጻሜ የሚያልፉ ክለቦች የሚለዩባቸው ናቸው።