ቀጥታ፡

በሻምፒዮንስ ሊጉ ሩብ ፍጻሜ የሚገቡ ቀሪ አራት ክለቦች የሚለዩባቸው ጨዋታዎች ይደረጋሉ 

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 9/2018 (ኢዜአ)፦  የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ መርሐ- ግብር ዛሬ ይጠናቀቃል። 

ባርሴሎና ከኒውካስትል ዩናይትድ ምሽት 2 ሰዓት ከ45 ላይ በካምፕ ኑ ስታዲየም ይጫወታሉ።


 

ሁለቱ ቡድኖች ከሳምንት በፊት በሴንት ጀምስ ፓርክ ስታዲየም ባደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ ተለያይተዋል።

ተመጣጣኝ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ በሚጠበቀው በዚህ ጨዋታ የሚያሸንፈው ቡድን ሩብ ፍጻሜውን ይቀላቀላል።

ሊቨርፑል ከጋላታሳራይ ምሽት አምስት ላይ በአንፊልድ ሮድ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።


 

ቡድኖች ከሳምንት በፊት በራምስ ፓርክ ስታዲየም ተገናኝተው ጋላታሳራይ 1 ለ 0 አሸንፏል። 

ሊቨርፑል ወደ ሩብ ፍጻሜ ለመግባት ከአንድ ጎል በላይ ልዩነት ማሸነፍ ይጠበቅበታል። 

ጋላታሳራይ ማሸነፍ ወይም አቻ መውጣት ስምንት ውስጥ እንዲገባ ያደርገዋል።

ባየርሙኒክ አተላንታን ምሽት አምስት ላይ በአሊያንዝ አሬና ስታዲየም ያስተናግዳል።


 

የጀርመኑ ቡድን በመጀመሪያው ጨዋታ 6 ለ 1 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፏል። ወደ ሩብ ፍጻሜ የመግባት እድሉ ከፍተኛ ነው።

አተላንታ በሂሳባዊ ስሌት ሩብ ፍጻሜ የመቀላቀል እድሉ እጅጉን የጠበበ ነው። 

ምሽት አምስት ላይ ቶተንሃም ሆትስፐርስ ከአትሌቲኮ ማድሪድ ምሽት አምስት ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።


 

አትሌቲኮ ማድሪድ በመጀመሪያው ጨዋታ 5 ለ 2 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

የስፔኑ ክለብ ሩብ ፍጻሜ ለመግባት ቅርብ ነው። በአንጻሩ በውጤት ማጣት ቀውስ የሚገኘው ቶተንሃም ውጤቱን የመቀልበስ ከፍተኛ ዳገት ይጠብቀዋል።

ትናንት በተደረጉ የጥሎ ማለፍ የመልስ ጨዋታዎች ሪያል ማድሪድ፣ ፒኤስጂ፣ አርሰናል እና ስፖርቲንግ ሊዝበን ተጋጣሚዎቻቸውን በደርሶ መልስ ውጤት በማሸነፍ ሩብ ፍጻሜ ገብተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም