ቀጥታ፡

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከሃዋሳ ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 7/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 19ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ ሶስት ጨዋታዎች በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይካሄዳሉ።

ከረፋዱ አራት ሃዋሳ ከተማ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ይጫወታሉ።

 

ሃዋሳ ከተማ በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው 18 ጨዋታዎች 11ዱን ሲያሸንፍ ሽንፈት ያስተናገደው ሁለት ጊዜ ብቻ ነው። በቀሪ አምስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 33 ግቦችን ሲያስቆጥር 12 ግቦችን አስተናግዷል።

ሃዋሳ በ38 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።

ተጋጣሚው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በውድድር ዓመቱ ካደረጋቸው 18 ጨዋታዎች መካከል በ16ቱ ድል ሲቀናው የተሸነፈው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በቀሪ አንድ ጨዋታ አቻ ወጥቷል።

43 ጎሎችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ በተመሳሳይ 10 ግቦች ተቆጥረውበታል። ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ49 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ሃዋሳ ከተማ ካሸነፈ አራተኛ ተከታታይ ድሉን ያስመዘግባል። ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሶስት ነጥብ የሊጉን መሪነት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዳግም  መረከብ ያስችለዋል።

ጨዋታው ተመጣጣኝ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ድሬዳዋ ከተማ ከሸገር ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

 

በሊጉ ስድስት ጨዋታዎችን በድል የተወጣው ድሬዳዋ ከተማ 11 ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ አንድ ጨዋታ ነጥብ ተጋርቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 16 ግቦቹን ሲያስቆጥር 29 ጎሎች ተቆጥረውበታል።

ድሬዳዋ ከተማ በ19 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዟል።

ሸገር ከተማ በውድድር ዓመቱ ባካሄዳቸው 18 ጨዋታዎች 15ቱን አሸንፎ በአምስቱ ተሸንፎ አንድ ጊዜ አቻ ተለያይቷል። 31 ግቦችን ሲያስቆጥር 18 ጎሎች ገብተውበታል። ቡድኑ በ37 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል።

ድሬዳዋ ከተማ ከሶስት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።

አዲስ አዳጊው ሸገር ከተማ ካሸነፈ ተከታታይ ድሉን ያስመዘግባል።

ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ አርባምንጭ ከተማ ከባህር ዳር ከተማ ጋር ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።

አርባምንጭ ከተማ በ10 ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ባህር ዳር ከተማ በተመሳሳይ 10 ነጥብ በግብ ክፍያ በልጦ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
 

አርባምንጭ ከተማ በሊጉ ካሸነፈ 11 ጨዋታዎች አልፈዋል። ባህር ዳር ከተማ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዷል።

ሁለቱ ቡድኖች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም