ቀጥታ፡

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በድል ጉዞው ጥሏል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 6/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ24ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ኢትዮ ኤሌክትሪክ ነገሌ አርሲን 2 ለ 0 አሸንፏል።

በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ሀሰን ሁሴን ግቦቹን አስቆጥሯል።

ካሜሮናዊው የነገሌ አርሲ ተጫዋች ፓስካል ኢቡሲ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።

በሊጉ ሶስተኛ ተከታታይ ድሉን ያስመዘገበው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ37 ነጥብ ደረጃውን ከስድስተኛ ወደ አራተኛ ከፍ አድርጓል። በሊጉ ዘጠነኛ ድሉን አስመዝግቧል።

በውድድር ዓመቱ ስድስተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ነገሌ አርሲ በ38 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል። ቡድኑ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች አላሸነፈም።

ሁለተኛ ደረጃን ከሃዋሳ ከተማ የመረከብ እድሉን አልተጠቀመበትም።

በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ሌላኛው መርሐ-ግብር መቀሌ 70 እንደርታ እና ወላይታ ድቻ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።


 

መቀሌ 70 እንደርታ በ23 ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ቡድኑ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ድል አልቀናውም።

ወላይታ ድቻ በ27 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዟል።

ጨዋታዎቹን ተከትሎ 24ኛ ሳምንት ተጠናቋል።

ፕሪሚየር ሊጉ ኢትዮጵያ በ36ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔ በምታደርጋቸው የማጣሪያ ጨዋታዎች ምክንያት ይቋረጣል።

ውድድሩ መጋቢት 25 ቀን 2018 ዓ.ም በ25ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር እንደሚመለስ የሊጉ አክሲዮን ማህበር አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም