ማህበራዊ
የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳደር በገዜ ጎፋ ወረዳ የመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ አደረገ
Jul 25, 2024 95
ጂንካ፤ሐምሌ 18/2016 (ኢዜአ)፡- የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳደር በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የተለያዩ ድጋፎችን አደረገ። የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳደር በስሩ ያሉ ስድስት ወረዳዎችና አንድ ከተማ አስተዳደር በጋራ በመቀናጀት ነው ድጋፍ ያደረጉት። መዋቅሮቹ "ለወገን ደራሽ ወገን ነው" በሚል መሪ ሃሳብ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የተለያዩ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል። በዚህን ጊዜ የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማልኮን ጨምሮ ሌሎች የስራ ኃላፊዎችና የዞኑ ተወካዮች አደጋው በተከሰተበት ስፍራ በመገኘት ተጎጂ ወገኖችን አጽናንተዋል ። በአካባቢው በተከሰተው ድንገተኛ አደጋ በጠፋው የሰው ሕይወት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸው፣ በአደጋው ቤተሰቦቻቸውን በሞት ላጡ ወገኖቻችን መፅናናትን ተመኝተዋል። የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳደር እንዲሁም የከተማና የገጠር ወረዳ መዋቅሮች በመቀናጀት ከ1 ሚሊዮን 199 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የተለያዩ የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን አቶ ማዕከል ገልጸዋል። ዞኑ በአደጋው ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የሚያደርገውን ሰብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።   የጎፋ ዞን አስተዳደርን በመወከል ድጋፉን የተረከቡት አቶ ታደለ ያዕቆብ "የደቡብ ኦሞ ዞን አመራር አባላት ረጅም ርቀት በመጓዝ ሀዘናችንን ስለተካፈላችሁ በተጎጂዎች ስም እናመሰግናለን" ብለዋል። በአካባቢው የደረሰው ጉዳት አስከፊ መሆኑን ጠቁመው በአሁኑ ወቅት ተጎጂዎችን የማጽናናትና ሰብኣዊ ድጋፎችን የማድረግ ስራዎች በተቀናጀ መልኩ መቀጠላቸውንም ገልጸዋል።  
በጠሎ ወረዳ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ የተፈናቀሉ ወገኖችን የመደገፍ ስራ እየተከናወነ ነው
Jul 25, 2024 114
ቦንጋ፤ ሀምሌ 18/2016(ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በካፋ ዞን ጠሎ ወረዳ ሞዲዮ ጎምበራ ቀበሌ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ የተፈናቀሉ ወገኖችን የማስጠለል ስራ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ገለጸ ። የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ለማ መሰለ(ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ በካፋ ዞን ዴቻ ወረዳ ሞዲዮ ጎምበራ ቀበሌ ትናንት ምሽት በጣለው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት የመሬት መንሸራተት አደጋ ተከስቷል። አደጋው በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ማስከተሉን ጠቅሰው የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ሶስት ሰዎች መሞታቸውንና በአንድ ሰው ላይ የአካል ጉዳት ሲደርስ 24 ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን ገልፀዋል። በአደጋው ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን በአንድ ጊዜያዊ መጠለያ በማቆየት የሰብዓዊ የድጋፍ አቅርቦት ስራው በዞኑና በወረዳው መዋቅር መጀመሩን ጠቁመዋል።   አደጋው በተከሰተበት አካባቢ ያለና ከጠሎ ወደ ቦንጋ የሚወስደው የአስፓልት መንገድ በናዳው ሳቢያ ተዘግቶ የነበረ ቢሆንም ማህበረሰቡና የወረዳው አስተዳደር ባደረጉት ጥረት መንገዱን ለትራፊክ ክፍት ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል። የአደጋውን ስፋትና ጉዳት በመለየት ተጨማሪ ድጋፍ ለማቅረብ እንዲያስችል የክልሉ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ከፍተኛ ባለሙያዎች ወደ ስፍራው መንቀሳቀሳቸውን ገልፀው፣ ጉዳዩን በተመለከተ በቀጣይ ተጨማሪ መረጃ እንደሚሰጥም አብራርተዋል ። የዝናቡ ሁኔታ ቀጣይነት ያለው በመሆኑ ቅድመ ማስጠንቀቂያ በተሰጠባቸው አካባቢዎች ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች የአካባቢው አስተዳደር ወደሚያዘጋጀው ጊዜያዊ መጠለያ መግባት እንደሚጠበቅባቸውም መክረዋል። ተጨማሪ አደጋ እንዳይከሰት የማስጠንቀቅ ፣ ተጋላጭ ከተባሉ አካባቢዎች ራቅ ወዳሉ ቦታዎች ነዋሪዎችን የማስጠለል እንዲሁም ሰብዓዊ ድጋፍ የማቅረብና የማቋቋም ስራ ህብረተሰቡን በማሳተፍ መስራቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
ሚዲያ ብሔራዊ ጥቅምን ለዓለም ለማሳወቅ አይነተኛ መሳሪያ መሆኑ ተገለጸ
Jul 25, 2024 110
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 18/2016 (ኢዜአ)፦ ሚዲያ ብሔራዊ ጥቅምን ለዓለም ለማሳወቅ አይነተኛ መሳሪያ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ለስኬታማ ዲፕሎማሲ የመገናኛ ብዙሃን ሚና ዙርያ ለአዲስ ተሿሚ አምባሳደሮች ስልጠና ተሰጥቷል። በስልጠናው ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም፤ “የመገናኛ ብዙሃን ሚና በዓለም አቀፍ ግንኙነት፤ ስትራቴጂካዊ ተግባቦት ለስኬታማ ዲፕሎማሲ” በሚል ርዕስ ገለጻ አድርገዋል፡፡   የሚዲያን የተፅዕኖ አቅምና አያያዝን መገንዘብ ብሔራዊ ጥቅምን በአግባቡ ለማስረዳት ጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል። ውይይቱን የመሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በበኩላቸው፤ ዲፕሎማሲያዊ ተግባቦት የኢትዮጵያን ዓለም አቀፋዊ ተሰሚነት እና ተፅዕኖ ለማሳደግ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በመድረኩ ፈጣን እና ተለዋዋጭ በሆነው ዓለምአቀፋዊ አውድ ውስጥ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ከወቅታዊ አዝማሚያዎች ጋር በሚጣጣሙ የላቁ የማኀበራዊ ሚዲያ አውታሮች መደገፍ እንዳለባቸው መገለጹን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
ሊጉ በክልሉ ከ700  ሺህ በላይ ሴቶችን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለማሰማራት መዘጋጀቱን ገለፀ  
Jul 25, 2024 56
ሆሳዕና ፤ ሐምሌ 18/2016 (ኢዜአ)፡- በብልጽግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኢትዮዽያ ክልል የሴቶች ሊግ በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ700 ሺህ በላይ ሴቶችን ለማሰማራት መዘጋጀቱን አስታወቀ። ሊጉ " በጎነት ለእህትማማችነት ለትውልድ ግንባታ እና ለዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ሃሳብ ያዘጋጀው ክልል አቀፍ የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ዛሬ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው። በወቅቱም በፓርቲው የክልሉ የሴቶች ሊግ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ኤልሳቤት ሽመልስ እንደገለፁት፤ ሊጉ አባላትን በማሳተፍ በክልሉ እየተካሄደ የሚገኘውን የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲጠናከር ይሰራል። በዚህ ረገድ በክልሉ ዘንድሮ በሚካሄደው የበጎ ፍድ አገልግሎት ላይ ከ700 ሺህ በላይ ሴቶችን በማሰማራት አመርቂ ተግባራትን ለማከናወን መዘጋጀቱን ገልጸዋል። መድረኩ የተዘጋጀውም በክልሉ ሴቶች ሊግ አማካኝነት በክረምት ወራት በሚከናወኑ የበጎ ፈቃድ ተግባራት ዙሪያ በተሰናዳ ዕቅድ ላይ በመምከር የቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ታስቦ መሆኑን አስረድተዋል። ይህም ሴቶች በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ለውጥ ላይ ያላቸውን ሚና በማጠናከር ትርጉም ያለው ውጤት ለማስመዘገብ ያስችላል ብለዋል ። በተለይ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመምጣት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ በሌማት ትሩፋትና በሌሎች ዘርፎች ሴቶችን ከማሳተፍ በተጨማሪ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል። ሴቶች በክረምት በጎ ተግባርና በመሰል ዘርፎች እንዲሳተፉ በማድረግ የምግብ ዋስትናን እንዲያረጋግጡ ትኩረት መሰጠቱንም አክለዋል። በመርሐ ግብሩ ላይ በብልፅግና ፓርቲ የሴቶች ሊግ ምክትል ፕሬዚዳንትና የሴቶች ሊግ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ መስከረም አበበን ጨምሮ ከክልሉ ሴቶች ሊግ፣ ከማህበራትና ከተለያዩ አደረጃጀቶች የተውጣጡ አመራሮች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።  
የበጎ ፍቃድ ተግባር ሰዎችን ከማገዝና ከመደገፍም ባለፈ የሀገርን መልካም እሴቶች ለማጎልበት ወሳኝ  ነው
Jul 25, 2024 63
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 18/2016(ኢዜአ)፦የበጎ ፍቃድ ተግባር ሰዎችን ከማገዝና ከመደገፍም ባለፈ የሀገርን መልካም እሴቶች ለማጎልበት ወሳኝ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለጹ ፡፡ በዘንድሮው ክረምት ከሁሉም ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ ወጣቶች በወሰን ተሻጋሪ በጎ አገልግሎት ተግባር ተሳታፊ ሆነዋል። የዘንድሮ ወሰን ተሻጋሪ የክረምት በጎ ፍቃድ ከተጀመረበት ሰኔ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመዘዋወር በጎ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡   የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርም "በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ " በሚል መሪ ሃሳብ ለወጣቶቹ የምስጋና እና ዕውቅና ፕሮግራም አዘጋጅቷል። በዚሁ መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) የሀገር ልማትንና ብልጽግናን ለማፈጠንና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በመንግስት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ ሂደትም አጠቃላይ ህብረተሰቡና በተለይም ወጣቶች እገዛና ተሳትፏቸው ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል። የበጎ ፍቃድ ተግባር ሰዎችን ከማገዝና ከመደገፍም ባለፈ የሀገርን መልካም እሴቶች ለማጎልበት ወሳኝ መሆኑንም ጠቅሰዋል። በዘንድሮ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሚኒስቴሩ 21 ሚሊየን ወጣቶችን በ13 የተለያዩ ዘርፎች ማሰማራቱን ጠቅሰው በዚህም 53 ሚሊየን ዜጎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል።   ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን የመጣችው ወጣት ሊሊ ተስፋዬ፤ በነፃ አገልግሎቴ ተደስቻለሁ በቀጣይም አጠናክሬ እቀጥላለሁ ብላለች።   ከአፋር ክልል የተሳተፈችው ሀናን መሀመድ፤ በወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፊቃድ አገልግሎቱ ወገኖችን ከማገዝም ባለፈ የተለያዩ አስደናቂ ባህሎችንና ማራኪ አካባቢዎችን አይቸበታለሁ ብላለች። በመድረኩ ወጣቶቹ ላደረጉት በጎ ተግባር እውቅና እና የምስጋና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የማህበረሰቡን የአብሮነትና  የበጎነት እሴቶች የሚጠናክር ነው 
Jul 25, 2024 54
ጎንደር ፤ ሐምሌ 18/2016(ኢዜአ)፡- የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የማህበረሰቡን ነባር የአብሮነትና የበጎነት እሴቶች የሚጠናክር መሆኑን በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የክረምት በጎ ፈቃደኛ ተሳታፊዎችና ተጠቃሚዎች ተናገሩ፡፡ የዞኑ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በላይ አርማጭሆ ወረዳ ትክል ድንጋይ ከተማ በችግኝ ተከላ፣ በደም ልገሳና የአረጋውያን ቤት በማደስ ስራ ዛሬ ተጀምሯል፡፡ በመርሃ ግብሩ ላይ ደም በመለገስ የተሳተፈው ወጣት ሰማልኝ ምትኩ በሰጠው አስተያየት፤ ደም መለገስ ደም የሚያስፈልጋት የእናት ህይወት መታደግ በመሆኑ ትልቅ የአዕምሮ እርካታ ይሰጠኛል ብሏል፡፡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እርስ በእርስ የመረዳዳትና የማህበረሰቡን ነባር የአብሮነት እሴት በማስቀጠል እያገዘ እንደሆነም ተናግሯል። በቤት እድሳት ስራ የተሳተፈው ወጣት ገብረዮሃንስ አዲስ ዓለም በበኩሉ፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘመን ተሻጋሪ የሆነውን የአብሮነትና የመደጋገፍ እሴታችን መግለጫ መሆኑን ገልጿል። በዘንድሮ ክረምት በሰላም ግንባታ፣ በልማትና በማህበራዊ አገልግሎቶች በመሳተፍ የእውቀትና የጉልበት አስተዋጽኦ ለማበርከት መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡ ላለፉት 30 ዓመታት የኖርኩበት መኖሪያ ቤቴ ደጋፊ በማጣቴ ተጎድቶ ቢቆይም ዛሬ ለማደስ ግንባታ በመጀመሩ ደስታ ተሰምቶኛል ያሉት የትክል ድንጋይ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ የሻለም አያሌው ናቸው፡፡ በጋውን በፀሃይና በንፋስ ክረምቱን ደግሞ በዝናብ የማይመች ህይወት ያሳልፉ እንደነበር አስታውሰው፤ ባህላችን በሆነው መረዳዳትና መደጋገፍ መሰረት በማድረግ ለተደረገልኝ ድጋፍ አመሰግናለሁ ሲሉ ገልጸዋል። የላይአርማጭሆ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አስረሳው ደሴ እንዳሉት፤ በወረዳው በርካታ በጎ ፈቃደኞች የህዝቡን አብሮነት በሚያጠናክሩ በሰላም እሴት ግንባታና በአረጋውያን ቤት እድሳት ስራ ተሳታፊ እየሆኑ ነው። በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ ማህበራዊ አገልግሎት ወጣቶች ተደራጅተው የጉልበት አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው ያሉት ደግሞ የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ድግስ መለሰ ናቸው፡፡ በጎ ፈቃደኞችም በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና በአረንጓዴ አሻራ በማሳተፍ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ እየተተገበረ መሆኑን ገልጸዋል። በመርሃ ግብሩ የ637 የአቅመ ደካሞችና አረጋውያን መኖሪያ ቤት እድሳትና ጥገና ከማከናወንም በላይ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ይከናወናል ብለዋል። በጤናው ዘርፍ የወባና የኮሌራ በሽታዎችን መከላከልና ቁጥጥር ስራ፣ ደም በማሰባሰብ ለጤና ተቋማት ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱን አስረድተዋል። በትምህርት ዘርፍም 56 ሺህ ተማሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት በ195 ትምህርት ቤቶች ለመስጠትም እንዲሁ፡፡ እስከ መስከረም 2017 ዓ.ም አጋማሽ በሚዘልቀው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 512 ሚሊዮን ብር የሚገመት ነጻ የጉልበትና የእውቀት አስተዋጽኦ ለማበርከት ግብ መያዙን ገልጸዋል፡፡ በመርሃ ግብሩ ከየወረዳዎች የተውጣጡ አመራር አባላት፣ በጎ ፈቃደኞችና ሌሎችም ህብረተሰብ ክፍሎችን ተሳታፊ ሆነዋል።    
በጎፋ ዞን የመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች አስቸኳይ የህክምና ድጋፍ እየተደረገ ነው
Jul 25, 2024 114
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 18/2016 (ኢዜአ)፦በጎፋ ዞን በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ወገኖች አስቸኳይ የመድሃኒት አቅርቦትና የህክምና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ፡፡ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ወገኖች አስቸኳይ ምላሽ እየሰጠ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የህክምና አገልግሎቱንም በተመለከተ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ አስቸኳይ የመድሃኒት አቅርቦትና የህክምና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ ገልጸዋል። ለተጎጅዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በመንግስት ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው የጤና ሚኒስቴርም ለህክምና አስፈላጊውን ግብአት በማቅረብ ፈጣን አገልግሎት እየሰጠ ነው ብለዋል። አደጋው ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ተጎጅዎችን ለመርዳት በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን አስታውሰው፤ ግብረ ሀይል ተቋቁሞ መድሀኒትና ሌሎች የህክምና ግብዓቶች እንዲቀርቡ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል። በዚህ አደጋ የተጎዱና የተፈናቀሉ ወገኖችን በማገዝ ከመንግስት እገዛ በተጨማሪ ህብረተሰቡ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አድንቀው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ጠይቀዋል።    
ህብረተሰቡ የወንጀል ድርጊቶችን በመከላከል ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የሚያደርገው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል
Jul 25, 2024 57
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 18/2016 (ኢዜአ)፦ ህብረተሰቡ የወንጀል ድርጊቶችን በመከላከል ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ጥሪ አቀረበ፡፡ የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ በ2016 በጀት ዓመት አፈፃፀምና በ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ከማዕከል እስከ ወረዳ ካሉ የሥራ ሀላፊዎች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ የቢሮው ኃላፊ ሊዲያ ግርማ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት መዲናዋ ያስተናገደቻቸው ሀይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላት ትውፊታቸውን ጠብቀው በሰላም ተከናውነዋል፡፡ ህብረተሰቡ የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶችን በመከላከልና ወንጀለኞችን ለህግ በማቅረብ የነበረው ሚና የጎላ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ህብረተሰቡ ከሰላም ሰራዊቱ ጋር በመቀናጀት ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቡን ገልጸው፤ ህገ ወጥ የመሬት ወረራ ፣ የጦር መሳሪያና የገንዘብ ዝውውር እንዲሁም አዋኪ ድርጊቶችን መከላከል ተችሏልም ብለዋል፡፡ ህብረተሰቡ በቀጣይም የወንጀል ድርጊቶችን በመከላከል ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የመድረኩ ተሳታፊዎች ወይዘሮ ወይኒቱ ሰይድ እና አቶ ኤልያስ ደምሴ በበኩላቸው፤ ህዝቡን ያሳተፈ የሰላም ማስከበር ሥራ በማከናወን ዘላቂ ሰላም የተረጋገጠባት አዲስ አበባን እውን እናደርጋለን ብለዋል፡፡  
የኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤመሬቶች ወጣቶች ግንኙነትን የሚያጠናክር ምክክር ተካሄደ
Jul 25, 2024 108
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 18/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያና በተባበሩት አረብ ኤመሬቶች ወጣቶች መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር ተካሄደ። የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ፉአድ ገና ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የወጣቶች ሚኒስትር ሱልጣን አልኒያዲ ጋር ተወያይተዋል። በውይይቱም በኢትዮጵያና በተባበሩት አረብ ኤመሬቶች ወጣቶች መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል። በትምህርት፤በስፔስ ሳይንስና በቴክኖሎጂ ዙሪያ በትብብር ለመስራት ተስማምተዋል። ከዚህም ባሻገር በወጣት ለወጣት ግንኙነትና ልምድ ልውውጥ በጋራ ለመስራት ከስምምነት ደርሰዋል።   በትናንትናው ዕለት በኢትዮዽያና እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መካከል ይፋ በተደረገው የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ የዲጂታል ሥራ ክሂሎቶች ማሳደጊያ የትብብር ፕሮጀክት ላይም በትብብር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል። የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ፉአድ ገና ከብሪክስ የወጣቶች ጉባኤ ጎን ለጎን ከብሪክስ አባል አገራት የወጣት ሚኒስትሮች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት እያደረጉ እንደሚገኝ የምክር ቤቱ መረጃ ያመለክታል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ከዘላቂ ልማት ግቦች ጋር በማስተሳሰር ሊተገበር ይገባል-አቶ ጸጋዬ ማሞ
Jul 25, 2024 64
ሚዛን አማን ፤ሐምሌ 18/2016 (ኢዜአ)፦የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ከዘላቂ ልማት ግቦች ጋር በማስተሳሰር መተግበር እንደሚገባ በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፀጋዬ ማሞ አስገነዘቡ። "በጎነት ለእህትማማችነት፣ ለትውልድ ግንባታና ለዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ቃል የ2016 የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሚዛን አማን ከተማ ዛሬ ተካሄዷል። አቶ ፀጋዬ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለፁት፤ በጎነት በገንዘብ የማይተመን የሰው ልጅ ሰብዓዊ ተግባር ነው።   በበጎ ተግባር ሴቶች ያላቸውን ተፈጥሯዊ ግንባር ቀደም ሚና አደራጅቶ መምራት እንደሚገባ ገልጸው፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ከዘላቂ ልማት ጋር አስተሳስሮ ማከናወን ይገባል ብለዋል። በክረምት ወራት የሚሠሩ የበጎ አድራጎት ተግባራት የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥና የሥራ ባህልን በማሳደግ ዜጎችን ከተረጂነትን ለማላቀቅ በሚያስችል መልኩ እንዲተገበሩም አሳስበዋል። አብሮነትን ለማጠናከር፣ የመተጋገዝና የመረዳዳት ባህልን ቀጣይነት ባለው መልኩ መሥራት እንደሚገባ አቶ ጸጋዬ አስገንዝበዋል። ያለንን አቅም ሰብሰብ አድርገን ከተጠቀምን ከባድ የሚመስለውን ማንኛውንም ፈተና ተሻግረን ብልጽግናን ማረጋገጥ እንችላለን ሲሉም አስረድተዋል። የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሰብለፀጋ አየለ በክልሉ ከ150 ሺህ በላይ ሴቶችን ያሳተፈ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በክረምት ወራት እንደሚከናወን አስታውቀዋል።   ዛሬ በተካሄደው የመክፈቻ መርሃ ግብርም ለአቅመ ደካማ አረጋውያን እና ተማሪዎች የቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ገልጸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በክረምትና በበጋ ወቅቶች ተከፋፍሎ ዓመቱን ሙሉ በትኩረት እንደሚካሄድ አስረድተዋል። ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ ትዕግስት ደሴ በወሊድና በሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች ደም በማጣት ለሚጎዱ ዜጎች ደም መለገሳቸውን ገልጸዋል።   ደም መለገስ የጎንዮሽ ጉዳት ስለሌለው ሁሉም በሰብዓዊነት በመነሳሳት ልገሳ እንዲያደርግም ጠይቀዋል። ሌላዋ የመድረኩ ተሳታፊ ወይዘሮ ብዙነሽ ዘብዴዎስ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚደረግ ማንኛውም ተግባር ሌሎችን እንደሚጠቅም ገልጸው፣ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሴቶች በጓሮ አትክልት ልማት እንዲሳተፉ አግዛለሁ ብለዋል።   በሚዛን አማን ከተማ በተካሄደው ክልላዊ የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ ግብርም የችግኝ ተከላ፣ የከተማ ጽዳትና የደም ልገሳ ተካሄዷል። በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ዙሪያ የሴቶችን ተሳትፎ የሚያሳይ እንቅስቃሴም ተጎብኝቷል።  
ሴቶች ያላቸውን አቅም በመጠቀም እንደ ሀገር ለሚነደፉ የልማት እቅዶች ስኬታማነት ሊረባረቡ ይገባል
Jul 25, 2024 64
ሆሳዕና፤ሐምሌ 18/2016(ኢዜአ)፦ ሴቶች ያላቸውን አቅም በመጠቀም እንደ ሀገር ለሚነደፉ የልማት እቅዶች ስኬታማነት ሊረባረቡ እንደሚገባ በብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ሊግ ጽህፈት ቤት አሳሰበ። በብልጽግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶች ሊግ "በጎነት ለእህትማማችነት፤ ለትውልድ ግንባታና ለዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ሃሳብ ያዘጋጀው ክልል አቀፍ የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ዛሬ በሆሳዕና ከተማ ተካሄዷል። የሊጉ ምክትል ፕሬዚዳንትና የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ወይዘሮ መስከረም አበበ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ ሴቶች ያላቸውን አቅም በመጠቀም በመንግስት በሚነደፉ የልማት እቅዶችን ተግባራዊ በማድረግ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል። ይህም ሴቶች በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ላይ በመሳተፍ የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እየተከናወነ ያለው ተግባር እንደሚጠናክር አስረድተዋል። ልማቱ ከሚያስገኘው ዘርፈ ብዙ ጥቅም ባለፈ ከተረጂነት ለመውጣት የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙ ለማድረግ ልዩ ትኩረት መሰጠቱንም ተናግረዋል። የችግኝ ተከላን ጨምሮ ጽዱ አካባቢን ለመፍጠር የሚደረገውን ሁለንተናዊ ጥረት ማገዝ ጤናማና አምራች የሁኑ ዜጎችን ለማፍራት ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑንም አስረድተዋል። በዚህም ሴቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስፋፋትና በዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ረገድ በጎ ተጽዕኖ መፍጠር እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።   የክልሉ ሴቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ኤልሳቤት ሽመልስ በበኩላቸው፤ በክልሉ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ700 ሺህ በላይ ሴቶችን በማሳተፍ ዘርፈ ብዙ ስራ ለማስራት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል። በዚህም የአቅመ ደካሞችን ቤት የመጠገንና የመስራት፤ የሌማት ትሩፋት ስራን በማጠናከር ከተረጂነት ለመውጣት ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙ ሴቶችን የማበረታታት ስራዎች እንደሚከናወኑም አስረድተዋል። በክልሉ ሴቶችን በሁለንተናዊ የልማት ዕቅዶች በማሳተፍ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።   በመርሃ ግብሩ ላይ የተሳተፉት በሆሳዕና ከተማ የቦብቾ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ እንዳሻሽ ጸጋዬ እንደገለጹት፤ በሀገሪቱ የተወጠኑ የልማት እቅዶችን ተግባራዊ በማድረግ የተሻለች ሀገርን ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ረገድ ሴቶች ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳሉ። ''እኛ ሴቶች ያለንን ውስን የመሬት ሃብት በማልማት ራሳችንን በኢኮኖሚ ከመደገፍ ባለፈ ምርቱን ለገበያ በማቅረብ የኑሮ ውድነትን መቀነስ እንደምንችል ካለፉት ዓመታት ልምድ በተጨባጭ ማየት ችልናል'' ብለዋል። በመርሃ ግብሩ ላይም በክልሉ የሚገኙ የሴቶች ሊግ፣ የማህበርና የፌዴሬሽን ዘርፍ ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።      
በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የሚደረገው ድጋፍ በቅርበት እየተከናወነ ነው - ተስፋዬ ቤልጅጌ (ዶ/ር)
Jul 25, 2024 71
ሀዋሳ፤ ሐምሌ 18/2016(ኢዜአ)፦በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ቤተሰቦቻቸውን ላጡና ለተፈናቀሉ ወገኖች አስቸኳይና ዘላቂ ድጋፍ ለማድረግ ሁሉም የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በቅርበት እየሰሩ መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጅጌ (ዶ/ር) ገለጹ። የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ ከአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽንና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሌሎች አካላት ጋር በመሆን በደቡብ ኢትዮጵያ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ ቤተሰቦቻቸውን ላጡና ለተፈናቀሉ ወገኖች በሚደረገው ሁለንተናዊ ድጋፍ ላይ ምክክር አድርገዋል። በዚህም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጅጌ(ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ አደጋው ከተከሰተ በኋላ በመንግስት በኩል ጉዳቱን ለመቀልበስ የተደረገው ጥረት አመርቂ መሆኑም ተገምግሟል። በአሁን ወቅት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጀምሮ በተሰጠው ትኩረት፣ የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽንና የጤና ሚኒስቴርን ጨምሮ ሁሉም የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በሥፍራው በመገኘት በቅርበት እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል። በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡ ወገኖችን አስከሬን የማውጣትና በሥርዓት እንዲቀበሩ የማድረጉ ተግባር አሁንም በርብርብ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ጉዳት የደረሰባቸውን ሕክምና የሚሹ ሕፃናትና ሌሎች ወገኖችን በመለየት አፋጣኝ ህክምና እየተሰጣቸው መሆኑን ገልፀው፤ የዕለት ደራሽ ምግብና መጠለያ ድጋፍም እንዲሁ በተደራጀ መልኩ እየቀረበ መሆኑን አውስተዋል። አደጋው ከደረሰበት ዕለት ጀምሮ በተለይ የነፍስ አድንና ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎችን የማውጣት ሥራው በርብርብ የተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፤ በአካባቢውና በመልክዓ ምድሩ ሁኔታ በሰው ኃይል ብቻ ለመስራት ግድ ማለቱን ጠቅሰዋል። ቦታው ማሽነሪዎችንና ተሽከርካሪዎችን ወደ ሥፍራው ለማስገባት አመቺ እንዳልሆነ ጠቁመው፤ በአካባቢው ማሽነሪዎችና ተሽከርካሪዎች በማንቀሳቀስ ጫና መፍጠር ዳግም የመሬት መንሸራተት አደጋ ሊያስከትል የሚችል መሆኑን ከባለሙያዎች በተሰጠ መረጃ መሰረት በሰው ሃይል ብቻ እንዲሰራ መደረጉን ተናግረዋል። ለአደጋው ምላሽ ለመስጠት የመንግስት መዋቅሮችን ጨምሮ ሁሉም የኢትዮጵያዊ ማንነትን በውል በሚገልፅ መልኩ ርብርብ እያደረጉ መሆኑን አብራርተዋል። በአደጋው የተጎዱ ወገኖችን በዘላቂነት የማቋቋሙ ሥራም ሆነ ተመሳሳይ አደጋ እንዳይከሰት የመከላከሉ ተግባር በትኩረት እንደሚሰራም አስረድተዋል። አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር ዶክተር ሺፈራው ተክለማርያም በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በአደጋው እስከ አሁን 226 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። በአሁኑ ወቅት በአደጋው ቤተሰቦቻቸውን ላጡና ለተፈናቀሉ ዜጎች አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች፣ የህክምናና ሌሎች ድጋፎች በበቂ ሁኔታ መኖራቸውን ጠቅሰዋል። አደጋውን በዘላቂነት ለመቀልበስ እንዲሁም ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን ከሥፍራው አንስቶ ወደ ሌላ አካባቢ ለማስፈር በቂ የዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውንም ገልፀዋል። በምክክሩ ላይ ከሁሉም የሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች እንዲሁም የሌሎች የፌዴራልና የክልል ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በበጎ ፈቃድ ለ20 ሺህ ዜጎች ነፃ የህክምና አገልግሎት ሊሰጥ ነው
Jul 25, 2024 87
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 18/2016(ኢዜአ)፦ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በክረምቱ የበጎ ፈቃድ ለ20 ሺህ ዜጎች ነፃ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀቱን አስታወቀ። የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፤ በሆስፒታሉ በመገኘት ችግኝ በመትከል አሻራቸውን አኑረዋል። በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግርም የጤና ባለሙያዎች በአካባቢ ጥበቃም ይሁን በማህበራዊ ጤና በቅንነት ማገልገል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። በመሆኑም የሆስፒታሉ ሰራተኞች በክርምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለጌርጌሴኖን የአእምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል የስነ-አዕምሮ ሕክምና ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አድንቀዋል። የበጎ ፈቃድ ስራ የዘወትር አገልግሎት ሆኖ በመቀጠል አቅመ ደካሞችን፣ ህፃናትንና እናቶችን የመደገፍ ስራም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል። የበጎ ፈቃድ ተግባራትን በማገዝና በመደገፍ ረገድ ጤና ሚኒስቴር የሚያደርገውን ድጋፍና እገዛ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ፤ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልና የጤና ሳይንስ ኮሌጁ በጤናው ዘርፍ የላቀ ሚናቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።   በመሆኑም ሆስፒታሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት የሚያበረክተው አስተዋጽኦም የላቀ በመሆኑ ባለሙያዎች ተባብርው ሚናቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል። የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፕሮፌሰር አንዷለም ደነቀ፤ ከዛሬ ጀምሮ "እሺ ለበጎ ተግባር" በሚል መሪ ሃሳብ ለአንድ ወር የሚቆይ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል። በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለ20 ሺህ ዜጎች ነፃ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት መታቀዱን ጠቅሰው በጌርጌሴኖን የአእምሮ ሕክምና ማዕከል ዘላቂ የሆነ የስነ-አእምሮ የሕክምና አገልግሎት እንሰጣለን ብለዋል። የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በመቄዶንያ የበጎ አድራጎት ማህበር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በዘላቂነት ዓመቱን ሙሉ እየሰጠ መሆኑ ተጠቅሷል።
ሀገር አቀፍ የወጣቶች ወሰን ተሻጋሪ የክረምት በጎ ፈቃድ ምስጋና መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው  
Jul 25, 2024 105
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 18/2016(ኢዜአ)፦ ሀገር አቀፍ የወጣቶች ወሰን ተሻጋሪ የክረምት በጎ ፈቃድ ምስጋና መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው። በዘንድሮው ክረምት ከ12ቱም ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ ወጣቶች በወሰን ተሻጋሪ በጎ አገልግሎት ተግባር ተሳታፊ ሆነዋል። ወጣቶቹ የዘንድሮ ወሰን ተሻጋሪ የክረምት በጎ ፍቃድ ከተጀመረበት ሰኔ 28 ቀን 2016 ዓ .ም አንስቶ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመዘዋወር የተለያዩ የበጎ ፍቃድ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡ ወጣቶቹ ላከናወኑት በጎ ተግባር የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር "በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ 3" በሚል መሪ ሃሳብ የምስጋናና ዕውቅና ፕሮግራም አዘጋጅቷል። በመድረኩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና ፣ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ወርቀሰሙ ማሞ፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እና ወጣቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። በዚሁ ወቅት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) የሀገር ልማትንና ብልጽግናን ለማፋጠንና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መንግስት በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ ውስጥ ወጣቱ ማህበረሰብ እያከናወነ የሚገኘው ሁለንተናዊ የበጎ ፍቃድ ተግባር ትልቅ ድርሻ እንዳለው ጠቅሰዋል። በጎ ፍቃድ የመልካም ስነ ምግባር መገለጫና ለማህበራዊ ትስስር መፈጠር ምቹ አጋጣሚ ነው ብለዋል ። አሁን ላይ በስፋት እየተተገበረ የሚገኘውና ማህበራዊ እሴቱ እየጎላ የመጣው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የጋራ ሃብታችንን በጋራ ለመጠቀምና ጠቃሚ እሴቶቻችን ለማጎልበት መሰረት ነው ነው ብለዋል ። የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት አካል የሆነው ወሰን ተሻጋሪ የክረምት በጎ ፍቃድ ወጣቶች የማህበረሰቡን መልካም እሴት እንዲቀስሙ ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም ጠቅሰዋል። የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በዘንድሮ ክረምት 21 ሚሊየን ወጣቶችን በ13 የልማት ዘርፎች ለማሰማራት ግብ ጥሎ እየሰራ እንደሚገኝ ነው የተገለጸው። በዚህም 53 ሚሊየን የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑና 19 ቢሊየን ብር የሚገመት አገልግሎት ለመስጠት ግብ መቀመጡን ሚኒስትሯ ጨምረው አስታውቀዋል። በመድረኩ ለወጣቶቹ የምስጋናና ዕውቅና ሰርትፊኬት እንደሚበረከትላቸው ከወጣው መርኃ ግብር ማወቅ ተችሏል። ከሌሎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር በቅንጅት እየተተገበረ ያለው የክረምት በጎ ፍቃድ ተግባር እስከ ክረምቱ ማብቂያ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል።    
የአረንጓዴ አሻራና የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በትውልድ ቅብብሎሽ ተጠናክረው  እንዲቀጥሉ የማህበራት ሚና ከፍተኛ ነው 
Jul 25, 2024 75
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 18/2016(ኢዜአ)፦የአረንጓዴ አሻራና የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በትውልድ ቅብብሎሽ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የማህበራት ሚና ከፍተኛ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ ገለጹ፡፡ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማት ጋር በመሆን የአረንጓዴ አሻራና የክረምት በጎ ፍቃድ ማስጀመሪያ መርኃ ግብር አካሂዷል፡፡ በመርኃ ግብሩ የሚኒስቴሩ ተጠሪ ተቋማት፣ የተለያዩ የስፖርት፣ የኪነ ጥበብና የስነ ጥበብ ማህበራት ተሳትፈዋል፡፡ በዚሁ ወቅት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ እንደተናገሩት ሚኒስቴሩ የሀገር ፍቅር በሚገለጽባቸው የበጎ ፍቃድ አገልግሎትና የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ላይ በስፋት በመሳተፍ ላይ ይገኛል፡፡   ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እነዚህ ተግባራት በትውልድ ቅብብሎሽ እንዲቀጥሉ ከስፖርት ፣ከኪነ ጥበብ፣ ሥነ ጥበብና ሌሎች ማህበራት ጋር በስፋት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህን ተከትሎ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአረንጓዴ አሻራና የክረምት በጎ ፍቃድ ማስጀመሪያ መርኃ ግብር ማካሄዱን ገልጸዋል፡፡ በመርኃ ግብሩ የችግኝ ተከላ፣ አነስተኛ ገቢ ላላቸው የተቋሙ ሰራተኛ ልጆች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍና የደም ልገሳ ተከናውኗል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በ2017 በጀት አመት ዘርፈ ብዙ የአረንጓዴ አሻራና የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡ በስፖርትና በኪነ-ጥበብ ዘርፍ የተሰማሩ ማህበራት የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብርና የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በትውልድ ቅብብሎሽ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተከትሎ ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ በጋራ እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ይህን ተከትሎ በቅርቡ በአማራ ክልል ማህበራቱን በማሳተፍ የችግኝ ተከላና የአቅመ ደካሞችን መኖሪያ ቤቶች የማደስና ተግባር ይከናወናል ብለዋል፡፡   የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ስፖርት ደጋፊዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ምንያህል ጌታቸው በበኩሉ ፤ ማህበሩ በአረንጓዴ አሻራ ልማት ከመሳተፍ ጎን ለጎን በስፖርቱ ድጋፍ ለሚፈልጉ ዜጎች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራ እያከናወነ መሆኑን ተናግሯል፡፡ በተለይም የሀገራቸውን ሠንደቅ አላማ ከፍ ያደረጉ ባለውለታዎች ችግር ባጋጠማቸው ወቅት ፈጥኖ በመድረስ የተለያዩ ድጋፎችን ማድረጉን በአብነት አንስቷል፡፡ እንደዚሁም አቅም ለሌላቸው ጀማሪ ስፖርተኞች የትጥቅና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ መሆናቸውን ጨምሮ ገልጿል፡፡ ማህበሩ በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት የአምስት አቅመ ደካማ ዜጎችን መኖሪያ ቤት የማደስ፣ የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍና በአዲስ አመት ለ 1 ሺህ 500 ዜጎች ማዕድ ለማጋራት መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡   የተቋሙ ሰራተኛና የመርኃ ግብሩ አስተባባሪ የሆነው አቶ ተዋበ መኮንን ከዚህ ቀደም በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራና የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ላይ በንቃት መሳተፋቸውን በማስታወስ ዘንድሮም የጀመሩትን ስራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጧል፡፡
ከጠለምት ወረዳዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን በመመለስ ሂደት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ተልዕኮውን በብቃት ተወጥቷል - የታዛቢ ቡድኑ አባላት
Jul 25, 2024 69
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 18/2016(ኢዜአ)፦ ከጠለምት ወረዳዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን በመመለስ ሂደት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ተልዕኮውን በብቃት መወጣቱን የአማራ እና ትግራይ ክልሎች የታዛቢ ቡድን አባላት ተናገሩ። ከሦስቱም የጠለምት ወረዳዎች ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎች ወደ ቀያቸው ሲመለሱ ማኅበረሰቡ በደስታ ተቀብሎ ሰላማዊ ኑሮ እንዲቀጥል መደረጉንም ተናግረዋል። የአማራ ክልል የጠለምት ወረዳዎች ተልዕኮ አፈፃጸም ታዛቢና ቅሬታ ሰሚ ዓባይ መንግስቴ፤ ከፌደራል መንግሥት እንዲሁም ከሁለቱ ክልሎች የተውጣጣ ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቋሞ የተፈናቀሉ ዜጎችን የመመለስ ሥራ መሥራቱን ገልፀዋል። የሁለቱ ክልሎች ታዛቢዎችና የሀገር ሽማግሌዎች በተገኙበት በሕዝባዊ ውይይት በቀጥታ የስም ዝርዝር አስተችቶ በማረጋገጥ ተፈናቃዮችን የመመለስ ሥራው በተሳካ መልኩ ተከናውኗል ብለዋል። በተፈናቃይና በተቀባይ ማኅበረሰብ መካከል የተናበበና የመረጃ ትክክለኛነት ተረጋግጦ ከሦስቱም የጠለምት ወረዳዎች ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ መደረጉን ተናግረዋል። የተፈናቀሉ ዜጎችን በመመለስ ሂደት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ተልዕኮውን በብቃት መወጣቱን አንስተው፤ በአካባቢው የሚነሱ ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ በመመለስ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት የተቀናጀ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ ትዝብታቸውን አጋርተዋል። በአካባቢው የነበሩ ታጣቂዎችን በማስወጣት መከላከያ ሠራዊት የአካበቢውን ሠላምና ደኅንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት እየተወጣ መሆኑን መታዘባቸውንም አረጋግጠዋል። በትግራይ ክልል የጠለምት ወረዳዎች ተልዕኮ አፈፃጸም ታዛቢ ታዘዘ ገብረ-ስላሴ፤ የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመመለስ መከላከያ ሠራዊት፣ የሁለቱ ክልሎች ተወካዮች፣ ከተፈናቃይና ተቀባዩ ማኅበረሰብ የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች በተገኙበት የጋራ መድረክ መካሄዱንአስታውሰዋል። በመድረኩ ላይ በተደረሰ የጋራ ስምምነት መሠረትም የመመለሱ ሂደት በተሳካ ሁኔታ ተከናውኗል ብለዋል። በዚህም ነጋዴው ወደንግዱ አርሶ አደሩ ወደእርሻ ስራው እንዲገባ መደረጉን መታዘብ እንደቻሉ አስረድተዋል። የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት በተጠናከረ መልኩ አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግና ለዘላቂ ሰላም በጋራ በመሥራት ልማትን ማስቀጠል እንደሚገባ የታዛቢ ቡድኑ አባላት አስገንዝበዋል። መንግሥትም በአካባቢው የሕክምና፣ የግብርና ግብዓትን ጨምሮ ሌሎችም መሠረታዊ አገልግሎቶችን የማሟላት ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል። በየአካባቢው ሰላምና ደኅንነትን ለማረጋገጥም ከኅብረተሰቡ የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆኑን አንስተዋል። የተፈናቀሉ ወገኖችን በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ በመመለስ ሂደት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላደረገው የላቀ አስተዋጽዖ ታዛቢዎቹ አድናቆትና ምስጋናቸውን አቅርበዋል።  
የክልሉን ሠላም ለማስጠበቅ  የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ድጋፋቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው ተገለጸ
Jul 25, 2024 68
ወልዲያ፤ ሐምሌ 18/2016(ኢዜአ)፦የአማራ ክልልን ሠላም በማስጠበቅ ዘላቂ ለማድረግ በየአካባቢው የሚገኙ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ድጋፋቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተገለጸ። ከሰሜን ወሎ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች የተሳተፉበትና በሠላም ማስከበር ዙሪያ የመከረ መድረክ በወልዲያ ከተማ ተካሄዷል። የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አራጌ ይመር በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት፤መንግስት የተሟላ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ህብረተሰቡን ባሳተፈ አግባብ ያለሰለሰ ጥረት እያደረገ ይገኛል። ለዚህም ይረዳ ዘንድ የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ትኩረት መሰጠቱን አስታውቀዋል።   መንግስት ለሠላም ያለው ቁርጠኝነት በተግባር እያሳየ መሆኑን አመልክተው፤ ለዘላቂ ሠላም መስፈን በየአካባቢው የሚገኙ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ድጋፋቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልጸዋል። የወልዲያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ የህዝብ ተሳትፎ አማካሪ አቶ ተስፋዬ ገብሬ በበኩላቸው፤ ችግሩን በሰላማዊ ውይይት ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የዚህ መድረክ ተሳታፊዎች "የሠላም አምባሳደር ልትሆኑ ይገባል'' ብለዋል። በምክክር መድረኩ የክልልና የዞን አመራር አባላት፣ ከዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ተሳታፊ ሆነዋል።    
የሐረርጌ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ፅህፈት ቤት ሰራተኞች በአሸዋ የገበያ ስፍራ በደረሰው አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ደጋፍ አደረጉ
Jul 25, 2024 61
ድሬዳዋ ፤ ሐምሌ 18/2016(ኢዜአ)፦ የሐረርጌ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ፅህፈት ቤት ሠራተኞች በድሬዳዋ አሸዋ ገበያ በደረሰው አደጋ የተጎዱ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም የሚውል ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸው ተገለፀ። በድሬዳዋ አሸዋ ገበያ በደረሰ የእሳት አደጋ የተጎዱ ወገኖችን በዘላቂነት የማቋቋም ስራ እንደቀጠለ ነው። የሐረርጌ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ፅህፈት ቤት ዳይሬክተር ጎሳ መንግስቱ (ዶ/ር) ዛሬ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ቤተክርስቲያኗ በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የተጎዱ ወገኖችን በመደገፍ ኃላፊነቷን እየተወጣች ትገኛለች። በድሬዳዋ አሸዋ የገበያ ስፍራ በደረሰው አደጋ የተጎዱ ወገኖችን ከማፅናናት ባሻገር የጽህፈት ቤቱ ሠራተኞች ከሐምሌ ወር ደሞዛቸው በማወጣት ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል። በዚሁ መሠረት ሰራተኞቹ 571 ሺህ ብር በማዋጣት ለወገን ደራሽ ወገን መሆኑን በተግባር አረጋግጠዋል ብለዋል። በቀጣይም አጋር ድርጅቶችን እና ለጋሾችን በማስተባበር አንገብጋቢ እና ቅድሚያ በሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል። የድሬዳዋ አስተዳደር ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ እና የገቢው አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሙሉካ መሐመድ በበኩላቸው የጽህፈት ቤቱ ሠራተኞችና አመራሮቹ ከደሞዛቸው በማዋጣት ያደረጉት ድጋፍ በአርአያነት የሚጠቀስና የሚመሰገን በጎ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል። ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚከናወኑ ስራዎች ስኬታማ እንዲሆን ኮሚቴው በአስተዳደሩ ከሚገኙ ተቋማት ጋር በስፋት እየተነጋገረ መሆኑን ገልፀዋል። ሌሎቹም ተቋማት ይህንን መንገድ በመከተል ወገኖቹን ለማቋቋም የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።      
የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንና ሌሎች የፌዴራል ከፍተኛ አመራር አባላት  በጎፋ ዞን ጉዳት ለደረሰባቸውን ወገኖች  እየተደረገ ባለው ምላሽ ዙሪያ እየመከሩ ነው
Jul 25, 2024 58
ጎፋ ሳውላ፤ ሐምሌ 18 /2016 (ኢዜአ)፡- የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንና ሌሎች የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ አመራር አባላት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች እየተደረገ ባለው የምላሽ ሥራ ላይ እየመከሩ ነው ። ምክክሩ እየተካሄደ የሚገኘው ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አደጋ ሥጋት ምክር ቤትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሆነ ተመላክቷል። በምክክሩ ላይ በአሁኑ ወቅት እየተደረገ ያለው አስቸኳይ የአደጋ ምላሽ ሥራ እየተገመገመ ይገኛል። እንዲሁም ተጎጂዎችን በቋሚነት ለማቋቋም ብሎም በጥናት ላይ ተመስርቶ ዳግም አደጋ እንዳይደርስ ለመከላከል በሚደረገው ተግባር ላይ ውሳኔዎች ይተላለፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። በምክክሩ ላይ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማሪያም(ዶ/ር) እና በህዝብ ተወካይች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጅጌ(ዶ/ር) በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ። በተጨማሪም ሌሎች የፌዴራል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ፣የክልልና የዞን አመራር አባላት ተገኝተዋል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም