በምዕራብ ወለጋ ዞን በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ10 ሺህ በላይ የአቅመ ደካማ ቤቶች ግንባታና እድሳት ይከናወናል

ጊምቢ፤ ሐምሌ 4/2017(ኢዜአ) ፡-በምዕራብ ወለጋ ዞን በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ10 ሺህ በላይ የአቅመ ደካማ ቤቶች ግንባታና እድሳት ለማከናወን ወደ ተግባር መገባቱን የዞኑ ሴቶችና ህፃናት ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታቀ።

በጽህፈት ቤቱ የሴቶች ንቅናቄና ተሳትፎ የማስፋት ቡድን መሪ አቶ ኤፍሬም ጃለታ፣ በዞኑ በዘንድሮ በጎ ፈቃድ አገልግሎት የአረንጓዴ አሻራ፣ የአቅመ ደካሞች ቤት ዕድሳትና ግንባታ፣ የማጠናከሪያ ትምህርት፣ ደም ልገሳ፤ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍና ሌሎች ተግባራት  እየተከናወኑ  መሆኑን  ገልጸዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራውን ለማሳካትም ወጣቶችን ጨምሮ ለሁሉም ባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ተሰርቷል ብለዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ለማሳካትም የዞኑ ወጣቶችና ሴቶች አደረጃጀቶችን ጨምሮ አቅም ያላቸው ነዋሪዎች እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።

በዞኑ ባለፉት ዓመታት  በተከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎች የበርካታ ሰዎችን ህይወት ከችግር ማውጣት መቻሉን አንስተዋል፡፡ 

ይህንን በበለጠ በማጠናከር  ከ6 ሺህ 489 በላይ ያረጁና 4 ሺህ 326 አዲስ  የአቅመ ደካማ ቤቶች ግንባታና እድሳት ለማከናወን ወደ ተግባር መገባቱን አስታውቀዋል።

በአጠቃለይ በዚህ ክረምት ወራት በዞኑ በተለያዩ የልማት ዘርፎች በሚከናወን የበጎ ፈቅድ አገልግሎት ይወጣ የነበረን ከፍተኛ የመንግስት ገንዘብ መታደግ ይቻላል ብለዋል።

በክረምቱ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራው ከሚሳተፉት መካከል ወጣት ዱላ ቸርነት፤ በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የተቸገሩ ወገኖችን በማገዝ የዜግነት ግዴታውን ለመወጣት መዘጋጀቱን ገልጿል።


 

በበጎ ፈቃድ የሚከናወኑ ስራዎች ላይ በመሰማራት ሀገርንና የተቸገሩ ወገኖችን ማገልገል ደስታ የሚሰጥ ተግባር እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡ 

በዞኑ በየዓመቱ የሚከናወኑ  የክረምት ወቅት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ ሲሳተፍ መቆየቱን የተናገረው ደግሞ የጊምቢ ከተማ ነዋሪ ወጣት አለማየሁ ዳቃ ነው፡፡


 

በዚህ ክረምትም ከሌሎች ወጣቶች ጋር በመሆን በተለያዩ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎች ለመሳተፍ መዘጋጀቱን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም