የተጀመሩ የሰላምና የልማት ተግባራትን ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ ነው

ገንዳ ውሃ ፤ ሐምሌ 3/2017(ኢዜአ)፦ የተጀመሩ የሰላምና የልማት ተግባራትን በማጠናከር የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን አስተዳደር አስታወቀ።

በዞኑ ባለፈው በጀት ዓመት የተሰሩ የሰላምና ልማት ስራዎችን የሚገመግምና በቀጣይ ስለሚሰሩ ተግባራት አቅጣጫ የሚያስቀምጥ መድረክ በገንዳ ውኃ ከተማ ተካሄዷል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እያሱ ይላቅ እንዳሉት የዞኑን ፀጋ አሟጦ በመጠቀም የህዝቡን የሰላምና ልማትና ስራዎች ተጠቃሚ ለማድረግ በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው።


 

በአካባቢያቸው ያጋጠመን የጸጥታ ችግሮች ከመፍታት ጎን ለጎን ልማትን ለማፋጠንና የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት መሰራቱን አውስተዋል።

ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በተካሄደው ጥረትም የዞኑ ህዝብ የነቃ ተሳትፎ አሁን በዞኑ ለሰፈነው ሰላም ሚና መጫወቱንም አስረድተዋል።

የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ደሳለኝ አያና በበኩላቸው በችግር ውስጥ ሆነው ተማሪዎችን ተቀብለው ያስተማሩ ትምህርት ቤቶችን በማጠናከርና በቀጣይ ያልጀመሩትን ለማስጀመር በቁርጠኝነት ይሰራል ብለዋል።


 

በዞኑ የትምህርት ገፅታን ለማሻሻልና የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ ከህብረተሰብ ተሳትፎና ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

ባለፈው ዓመት በርካታ የህዝብ ለህዝብ ውይይቶች ተደርገው የህዝቡን ሰላምና ልማት የማረጋገጥ ተግባር መከናወኑን የገለፁት ደግሞ በብልፅግና ፓርቲ የዞኑ ፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ ደመቅ አበበው ናቸው።

በዞኑ አብዛኞቹ ቀበሌዎች ወደ ሰላም መመለስ መቻላቸውን አስረድተው ሰላምን በዘላቂነት በማፅናት የፀጥታና የልማት ሰራዎች በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚሰሩም አመልክተዋል።


 

የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አየለ አናውጤ (ዶ/ር) እንዳሉት በክረምት ወቅት ከመደበኛ ስራዎች ጎን ለጎን የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ማሳለጥ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የዞኑን አንፃራዊ ሰላም ወደ ተሟላ ሰላም ለማሸጋገር የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መመለስ እንደሚገባም አፅንኦት ሰጥተዋል።

ከግምገማ መድረኩ ጎን ለጎንም የደም ልገሳ መርሃ ግብር ተካሄዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም