በበጀት ዓመቱ ከበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ከ423 ሺህ በላይ ዩኒት ደም ተሰብስቧል - አገልግሎቱ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2017(ኢዜአ)፦ በተጠናቀቀው የ2017 በጀት ዓመት ከበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ከ423 ሺህ በላይ ዩኒት ደም መሰብሰቡን የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

ባንኩ በሁለት ወር የክረምት የበጎ ፈቃድ ደም ልገሳ መርሃ-ግብር 70ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ማቀዱንም ገልጿል፡፡

የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሃብታሙ ታዬ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በአዲስ አበባና በክልሎች የደም ልገሳ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በስፋት ተከናውኗል።

በትምህርት ቤቶች የደም ልገሳ ክበቦችን በማቋቋም የተማሪዎችን ግንዛቤ የማሳደግ ሥራ በትኩረት መሰራቱንም እንዲሁ።

የግንዛቤ ፈጠራ ስራውን ተከትሎ ከጊዜ ወደ ጊዜ ስለ ደም ልገሳ ያለው አመለካከት ለውጥ እየታየበት እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡


 

በዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ423ሺህ በላይ ዩኒት ደም መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ይህም ከጊዜ ወደ ጊዜ በበጎ ፍቃደኝነት ደም ለመለገስ የሚመጡ ስዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የሚያሳይ መሆኑን አመላክተዋል።

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም በሁለት ወራት የክረምት የበጎ ፈቃድ ደም ልገሳ መርሃ-ግብር 70ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ መታቀዱንና በቂ ዝግጅት መደረጉን አንስተዋል።

የደም ልገሳ ተግባር የሰዎችን በተለይም የእናቶችን ህይወት መታደግ በመሆኑ ህብረተሰቡ ደም መለገስን ባህል በማድረግ ህይወት እንዲታደግ ጥሪ አቅርበዋል።

በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሽ የሆኑት ወይዘሮ አሰጋሽ ጎሳ ለ121ኛ ጊዜ ደም መለገሳቸውን ጠቁመው፤ በዚህም ህይወት እየታደጉ በመሆኑ የሕሊና እርካታ እንደሚሰማቸው አመልክተዋል።

በአሁኑ ሰዓት በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለው ደም የመለገስ ልምድ እየዳበረ መምጣቱን የተናገሩት ደግሞ ለ81ኛ ጊዜ በበጎ ፈቃድ ደም መለገሳቸውን የገለጹልን አቶ ሞገስ በዳኔ ናቸው፡

ማንኛውም ሰው በደም እጦት ምክንያት እንዳይጎዳ በጎፈቃደኛ ለጋሾች ደም እንዲለግሱ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም