ኢትዮጵያ ያሏትን የቱሪዝም ፀጋዎች ለአለም በማስተዋወቅ የዘርፉን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ያስፈልጋል - የዘርፉ ባለሙያዎች

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2017(ኢዜአ) ፡-ኢትዮጵያ ያሏትን የቱሪዝም ፀጋዎች ለአለም በማስተዋወቅ የዘርፉን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎች ገለፁ።

በኢትዮጵያ በአገር በቀል ሪፎርሙ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰሩ ካሉ አምስት የኢኮኖሚ ምሰሶዎች መካከል አንዱ ቱሪዝም ነው።

የአዳዲስና ነባር የቱሪዝም መዳረሻዎች ልማት እየተከናወነ ሲሆን ዘርፉ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን ሚና ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

ይሄንንም በማስመልከት አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የቱሪዝም ባለሙያዎች እንዳሉት መንግስት የሰጠው ትኩረት ለዘርፉ ከፍተኛ መነቃቃትን መፍጠር ችሏል።

የታላቁ ኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶች ማህበር አባልና የፕሌዠር ኢትዮጵያ አስጎብኚና የጉዞ ወኪል ባለቤት ናሆም አድማሱ እንዳሉት ኢትዮጵያን በቱሪዝም ዘርፍ የበለጠ ከፍ ማድረግ የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል።


 

ሀገሪቱ ያላትን  በርካታ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የመስህብ ቦታዎች በማስተዋወቅና መልካም መስተንግዶን ለጎብኚዎች በመስጠት ከዘርፉ የሚገኘውን ተጠቃሚነት ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል።

የጉዞና ጉብኝት ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም በበኩሉ በአሁኑ ሰዓት መንግስት ከመቼውም ጊዜ በላይ ለቱሪዝም ዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ  መስራቱን ተናግሯል።


 

የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ስራዎች በመላው ሀገሪቱ እየተከናወኑ መሆናቸውንና ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ለቱሪዝም መነቃቃት አስተዋፅኦ እያበረከቱ መሆኑን ተናግሯል። 

ለቱሪስቶች ምቹ ሁኔታን መፍጠር የሚያስችሉ የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የአዲስ አበባ ሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያዎች ማህበር ኤክስክዩቲቭ አባል ወንድምዬ አዋሽ ናቸው።


 

ኢትዮጵያ ያሏትን የቱሪዝም ፀጋዎች ለአለም በማስተዋወቅ ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ ላይ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ጠንካራ የቱሪዝም ዲፕሎማሲ ያላት አገርን ለትውልድ ለማስተላለፍም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የቱሪዝም ዘርፉን ተጠቃሚነትና ዘላቂነት ለማረጋገጥ የዘርፉ ተዋንያን መልካም ስነምግባርን በመላበስ በቅንጅት መስራት ላይ ትኩረት እንዲሰጡም እንዲሁ። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም