በኢትዮጵያ ዘላቂና አካታች የምግብ ስርዓት ሽግግርን ለማሳካት የሁሉም ሚና ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2017(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ዘላቂ እና አካታች የምግብ ስርዓት ሽግግርን ለማሳካት የሁሉም አካላት ሚና ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር "ከራዕይ ወደ ተግባር፤ የኢትዮጵያ ዘላቂና አካታች የምግብ ስርዓት ሽግግር ጉዞ" በሚል መሪ ሀሳብ በኢትዮጵያ ሥርዓተ ምግብ ላይ ያደረገ ውይይት ተካሂዷል። 

በዚሁ ወቅት የመነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍሬው ተገኝ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ለዘላቂ የልማት ግቦች ስኬት የበኩሏን አስተዋጽኦ እያደረገች ትገኛለች። 

ኢትዮጵያ የምግብ ስርዓት ሽግግር ትግበራን በመጀመር ግንባር ቀደም ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።


 

2ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስርዓተ ምግብ ጉባኤ በኢትዮጵያ እና በጣሊያን አስተናጋጅነት ከሐምሌ 20 እስከ 22 ቀን 2017 በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

ጉባዔው በኢትዮጵያ መካሄዱ ለሀገር ገጽታ ግንባታ ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን ገልጸው፤ በተለይም ኢትዮጵያ ለጀመረችው የምግብ ስርዓት ሽግግር ጉዞ እውቅና የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በተለይም ከለውጡ ወዲህ የምግብ ስርዓት ሽግግርን የሚያፋጥኑ የተለያዩ ብሔራዊ ፕሮግራሞችን በመቅረጽ በትኩረት እየሰራች እንደምትገኝ ይታወቃል።

ለአብነትም የሌማት ትሩፋት፣ የስንዴ ልማት፣ አረንጓዴ አሻራ፣ የትምህርት ቤት ምገባ፣ ኢትዮጵያ ታምርት እንዲሁም የሰቆጣ ቃል-ኪዳን ኢንሼቲቮች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ የትምህርት ቤቶች ምገባ ኢኒሼቲቭ ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬዓለም ሺባባው በመድረኩ የኢትዮጵያ መንግስት የሰቆጣ ቃልኪዳን እና የተማሪ ምገባ ኢኒሼቲቮችን በመውሰድ ለትውልድ ግንባታ ትልቅ ሥራ እየሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡


 

በዚህም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ብቻ ከ8 መቶ ሺህ በላይ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ በመመገብ ላይ መሆኑን ተናግረው፤ በሰቆጣ ቃልኪዳንም ለትውልድ ግንባታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተፈጥሮ ሳይንስና ስነ ቀመር ኮሌጅ ዲን ቢቂላ ወርቅነህ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ግብርና ምርታማነት አቅምን ማሳደግ የሁሉም ሚና ነው ብለዋል፡፡


 

በተለይም የግሉ ሴክተር የሚጠበቅበትን መወጣት እንዳለበት አንስተው ወደ ምግብ ማቀነባበር እንዲሁም እሴትን የመጨመር ስራ መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

የኤንቢሲ ቴሌቪዥን ዋና ስራ አስፈጻሚ ብሩክ ከበደ፤ የምግብ ስርዓት እና የምግብ ሉዓላዊነት የመገናኛ ብዙሃን ዋነኛው አጀንዳ ነው ብለዋል፡፡ 


 

በተጨማሪም መገናኛ ብዙሃን በሀገራዊ ዋና ዋና ጉዳዮች ዙሪያ በርካታ ስራዎች መስራታቸውን ጠቁመው፤ ለአብነትም የአረንጓዴ አሻራ፣ የሌማት ትሩፋት እንዲሁም በግብርና መካናይዜሽን ዙሪያ በርካታ ስራዎች መሥራታቸውን ጠቁመዋል፡፡   

የኒው ላይፋ ቴን ቻሌንጅ ዴቬሎፕመንት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ሔለን ጥላሁን በበኩላቸው የምግብ ስርዓትን አሻጋሪና አካታች ለማድረግ ወጣቶችን፣ ሴቶችን እና አካል ጉዳተኞችን አሳታፊ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡      


 

በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብ ስርዓት ጉባዔን በስኬት ለማስተናገድ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም