በክልሉ በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች የበርካቶችን ሕይወት እየታደጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች የበርካቶችን ሕይወት እየታደጉ ነው

ወላይታ ሶዶ፤ሐምሌ 3/2017 (ኢዜአ))፡-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎ ፈቃደኛች በተከታታይ እያበረከቱት ያለው የደም ልገሳ የበርካቶችን ሕይወት እየታደጉ መሆኑ ተገለጸ።
የክልሉ ጤና ቢሮ የዓለም የደም ለጋሾ ቀንን ምክንያት በማድረግ ለበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾችና ተቋማት የምስጋና እና የእውቅና መርሃ ግብር ዛሬ በወላይታ ሶዶ ከተማ አካሂዷል።
ዕውቅና ከተሰጣቸው በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች መካከል ወጣት ሄኖክ ኮይራ በአርአያነት ተጠቅሷል።
ወጣቱ በአርአያነት የተጠቀሰውም ለ65 ተከታታይ ጊዜ በበጎ ፈቃደኝነት ደም በመለገሱ ሲሆን፤ለዚህም ከክልሉ ጤና ቢሮ የዕውቅናና ምስጋና የምስክር ወረቀት እንዲሁም ሜዳሊያ ተበርክቶለታል።
ወጣት ሄኖክ የሚለገሰው ደም በተለያዩ ምክንያቶች ደም የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ሕይወት እየታደገ መሆኑን ሲያስብ እና ሲመለከት የአዕምሮ እርካታ ከመስጠት ባለፈ ደስታ እንደሚሰማው ይናገራል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ለተከታታይ 65 ጊዜ ደም በመለገሱ የሰጠው እውቅና ልግስናውን ይበልጥ ለማጠናከር የሚያበረታታው መሆኑን ገልጿል።
ሌሎችም ወጣቶች የሚተካ ደም በመለገስ የማይተካ የሰው ሕይወት ቢታደጉ በህይወታቸው ይበልጥ ደስተኛ ሊሆኑ እንደሚችሉ አስተያየት ሰጥቷል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ በበኩላቸው፤ ወጣት ሄኖክ ኮይራን ጨምሮ በበጎ ፈቃድ ደም የሚለግሱ አካላት የበርካቶችን ሕይወት እየታደጉ በመሆናቸው ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል።
ቢሮው የሕብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የለጋሾች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ተናግረዋል።
በበጎ ፈቃድ ደም በመለገስ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ አካላትን ዕውቅና የመስጠት ስራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ሃላፊው አስታውቀዋል።