ሰራዊቱ የሀገር ሉዓላዊነትን ከማስከበሩ በተጓዳኝ ማህበራዊ አገልግሎቶች ላይ እየተሳተፈ አጋርነቱን አጠናክሮ ቀጥሏል

ጅማ ፤ሐምሌ 3/2017(ኢዜአ)፡-  ሰራዊቱ የሀገር ሉዓላዊነትን ከማስከበር መደበኛ ስራው በተጓዳኝ ማህበራዊ አገልግሎቶች ላይ በንቃት እየተሳተፈ  አጋርነቱን  አጠናክሮ  መቀጠሉን  የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ዘውዱ በላይ ገለጹ።

የዳሎል ማእከላዊ ዕዝ ሰራዊት አባላት ባለፉት አስር ቀናት ሲያካሄዱ የቆዩት ስፖርት ፌስቲቫል ውድድር ማጠቃለያ እና ደም ልገሳ መርሃ ግብር ዛሬ አካሄደዋል።


 

በዚህ ወቅት የዳሎል ማዕከላዊ እዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል  ዘውዱ በላይ፤  ሰራዊቱ የሀገር ሉዓላዊነትን የማስከበር መደበኛ ስራውን በብቃት እየፈጸም በጀግንነት መቀጠሉን ተናግረዋል። 

በተጓዳኝም በማህበራዊ አገልግሎቶች ላይ በንቃት በመሳተፍ  አጋርነቱን እያጠናከረ መቀጠሉን ገልጸው፤ የዕዙ አባላት በዚህ ረገድ አበረታች እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን አስታውቀዋል።

የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝም ተልዕኮን ለመፈጸም በተሻለ ዝግጁነት ላይ እንደሚገኝ ያመለከቱት ዋና አዛዡ፤ በቀጣይም በአካላዊ ብቃትና ስነ ልቦናዊ ዝግጅነቱ ይበልጥ  እንደሚጠናከር አስረድተዋል።

ዛሬ የተጠናቀቀው የስፖርት ፌስቲቫልም ሰራዊትና ስፖርት የማይለያዩ ተግባራት መሆኑን ተረድተው ለውድድሩ መሳካት አስተዋጽኦ ያበረከቱ አካላት ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል።

የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኮሎኔል በዛብህ ይመር በበኩላቸው፤ የሰራዊቱን ብቃት ይበልጥ ለማጎልበት  ያለመ የስፖርት ውድድር መካሄዱን ተናግረዋል።

በዕዙ ስር የሚገኙ  ኮሮች በስፖርታዊ ውድድሩ መሳተፋቸውን አንስተው፤ ውድድሩም የተሳካ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

የጅማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ጠሃ ቀመር በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤  ዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ በአካባቢው ሰላም ፀንቶ እንዲቀጥል  የማይተካ ሚና እየተወጣ ነው ብለዋል።

የዕዙ  ስራ የበለጠ እንዲቃና አስተዳደሩ የሚጠበቅበትን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

በመዝጊያ መርሃ ግብሩ ላይ የሰራዊቱ ከፍተኛ መኮንኖች፣ የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚዳንት አቶ ዛዲግ አብረሃ፣ የጅማ ዞን አስተዳደሪ አቶ ቲጃኒ ናስር እና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም