በክልሉ የሚያጋጥሙ በሽታዎችን ፈጥኖ በመለየት ምላሽ መስጠት የሚያስችል የጤና ስርዓት የመዘርጋት ስራ ይጠናከራል

ባህርዳር፤ ሐምሌ 4/2017(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በየጊዜው የሚያጋጥሙ በሽታዎችን ፈጥኖ በመለየት ምላሽ መስጠት የሚያስችል የጤና ስርዓት የመዘርጋት ስራ እንደሚጠናከር በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ(ዶ/ር) ገለጹ።

በአማራ ክልል ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚተገበር "የጤና ደህንነት ትግበራ /health security activity/" የተሰኘና የህብረተሰቡን ጤንነት የሚያስጠብቅና የሚያሻሽል ፕሮጀክት ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ይፋ ተደርጓል።


 

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ፣ የክልሉ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ(ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት በክልሉ የጤና ስርዓቱን ለማሻሻል የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው።

በዛሬው እለት ይፋ የተደረገው ፕሮጀክትም በክልሉ በየጊዜው የሚያጋጥሙ የጤና ችግሮችን ለይቶ መፍታት የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።

ፕሮጀክቱ የበሽታ ቅኝት በማድረግ፣ በፍጥነት በመለየትና ለሚመለከተው አካል በማሳወቅ አፋጣኝ መፍትሄ ለመስጠት አጋዥ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ የታለመለትን ግብ እንዲመታ የክልሉ መንግስትና ህዝብ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር ያደርጋሉ ብለዋል።


 

የአማራ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ፤ ፕሮጀክቱ በክልሉ በተመረጡ 56 ወረዳዎች የሚተገበር ነው ብለዋል።

በክልሉ በጤናው ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የቤተ ሙከራ አቅምን ማሳደግና የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ማጎልበት ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አስረድተዋል።


 

"የጤና ደህንነት ትግበራ /health security activity/" ፕሮጀክት ምክትል ኃላፊ ዶክተር ኤልያስ ዋለልኝ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የአማራ ክልልን ጨምሮ በአፋርና በትግራይ ክልሎች የሚተገበር መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ፕሮጀክቱ ከሰው ወደ ሰው፣ ከእንስሳት ወደ ሰው፣ ከሰው ወደ እንስሳትና ከአካባቢ ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎችን አስቀድሞ በሚካሄድ ቅኝት በመለየት ለመከላከል አልሞ የሚሰራ ነው ብለዋል።

በመድረኩ የክልልና የፌደራል የጤናው ዘርፍ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም