የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከህሊና እርካታ ባለፈ ማኅበራዊ ትስስር እያጎለበተ መጥቷል - አቶ መለስ አለሙ

ሐረር፤ ሐምሌ 4/2017(ኢዜአ)፦ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከህሊና እርካታ ባለፈ ማኅበራዊ ትስስርን እያጎለበተ መምጣቱን በብልፅግና ፓርቲ የዋና ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ መለስ ዓለሙ ተናገሩ። 

በኦሮሚያ ክልል አምስት ሚሊዮን ሴቶች የሚሳተፉበት የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በማያ ከተማ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።

በፕሮግራሙ ማስጀመሪያ ላይ የተገኙት በብልፅግና ፓርቲ የዋና ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ መለስ ዓለሙ እንደገለጹት በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሴቶችና ወጣቶች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች የሚሳተፉበት የተለያዩ ተግባራት ይከናወናሉ።


 

በፕሮግራሙ የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላን ጨምሮ የአቅመ ደካማ መኖሪያ ቤቶች እድሳት፣ የድጋፍና እንክብካቤ እንዲሁም ሌሎች ስራዎች ይከናወናሉ ብለዋል።

እነዚህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ከህሊና እርካታ ባለፈ ወንድማማችነትንና ማህበራዊ ትስስርን እያጠናከሩ በመምጣታቸው  ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የሴቶች ክንፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሳሚያ አብደላ እንደገለጹት በክልሉ አምስት ሚሊዮን ሴቶች የሚሳተፉበት የክረምት በጎ ፈቃድ ተግባራት ተጀምረዋል።


 

በመርሃ ግብሩም የአቅመ ደካማ መኖሪያ ቤት እድሳት፣ የደም ልገሳ፣ ማዕድ ማጋራት፣ የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላን ጨምሮ 11 የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች እንደሚከናወኑ ገልጸው ይህም ሴቶች እርስ በእርስ እንዲደጋገፉ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።

በኦሮሚያ ክልል የማያ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታደለ ንጉሴ በበኩላቸው በከተማ መስተዳድሩ በሚከናወነው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ300 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች በ34 የክረምት በጎ ፈቃድ ተግባራት እንደሚሳተፉ ጠቁመዋል።


 

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎች ህብረተሰቡን እየደገፈና የወጣቶችን ተሳትፎና የመረዳዳት ባህልና እሴትን እያጎለበተ መምጣቱን ገልጸዋል።

ከታማሚ ልጃቸው ጋር በፈረሰ ቤታቸው ውስጥ ሲኖሩ ለችግር ተጋልጠው እንደነበር ያስታወሱት ደግሞ በማያ ከተማ አስተዳደር የአደሌ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ዙቤዳ ቃሲም ናቸው። 


 

አሁን ላይ ይህን ችግራቸውን የበጎ ፈቃደኞች ተመልክተው ቤታቸው በማደሳቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።

መኖሪያ ቤታቸው ከማርጀቱ የተነሳ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ለህይወታቸው ይሰጉ እንደነበር የገለጹት ደግሞ ሌላው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጠቃሚው አቶ ሸሪፍ ኢብራሂም ናቸው።


 

ይህን ችግራቸውን በመረዳት የማያ ከተማ መስተዳድርና ነዋሪዎች ቤታቸውን በመገንባታችው መደሰታቸውን ተናግረዋል።

በፕሮግራሙ የብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍና ሌሎች የፌደራልና የክልል የብልፅግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ አመራሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም