መንግሥት በሰቆጣ ቃል ኪዳን እና በትምህርት ምገባ መርሐ ግብር ለትውልድ ግንባታ አመርቂ ስራዎችን እያከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መንግሥት በሰቆጣ ቃል ኪዳን እና በትምህርት ምገባ መርሐ ግብር ለትውልድ ግንባታ አመርቂ ስራዎችን እያከናወነ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2017(ኢዜአ)፦መንግሥት በሰቆጣ ቃል ኪዳን እና በትምህርት ምገባ መርሐ ግብር ለትውልድ ግንባታ አመርቂ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ የትምህርት ቤቶች ምገባ ኢኒሼቲቭ ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬዓለም ሽባባው ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር "ከራዕይ ወደ ተግባር፤ የኢትዮጵያ ዘላቂና አካታች የምግብ ስርዓት ሽግግር ጉዞ" በሚል መሪ ሀሳብ በኢትዮጵያ ሥርዓተ ምግብ ላይ ያተኮረ ውይይት አካሂዷል፡፡
በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ የትምህርት ቤቶች ምገባ ኢኒሼቲቭ ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬዓለም ሽባባው እንዳሉት፥የኢትዮጵያ መንግስት ትልልቅ ኢኒሼቲቮችን በመቅረፅ ለትውልድ ግንባታ በርካታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ከዚህም ውስጥ የትምህርት ቤት ምገባ እና የሰቆጣ ቃል ኪዳን ተጠቃሽ መሆናቸውን ያነሱት ዳይሬክተሯ፤ ከቅድመ መደበኛ እስከ 8ኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች የምገባ መርሐ ግብር እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቀን ሁለት ጊዜ ከ800 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመመገብ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመው፤ ከ13ሺህ በላይ ለሆኑ እናቶችም የስራ ዕድል መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡
የምገባ መርሃ ግብሩ መንግስት የተገበራቸው ትልልቅ ኢኒሼቲቮች ውጤታማ መሆናቸውን አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም የተማሪዎች መጠነ ማቋረጥና ማርፈድ ማስቀረት ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡
በሰቆጣ ቃልኪዳን ህጻናት ከጽንስ ጀምሮ ተመጣጣኝ ምግብ እንዲያገኙ በማስቻል የነገዋን ኢትዮጵያ በመገንባት ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡
የሰቆጣ ቃልኪዳን በማስፋፋት ምዕራፍ ትግበራው በ2017 በጀት ዓመት በ334 ወረዳዎች የተተገበረ ሲሆን በዚህም በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሚያጠቡና ነፍሰጡር እናቶች እንዲሁም በርካታ ህጻናት ተጠቃሚ መሆናቸው ይታወቃል።