በዞኑ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ16 ሺህ በላይ የተለያዩ የታዳሽ ሃይል አማራጮች ለማህበረሰቡ እንዲቀርቡ ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ16 ሺህ በላይ የተለያዩ የታዳሽ ሃይል አማራጮች ለማህበረሰቡ እንዲቀርቡ ተደርጓል

ወልዲያ ፤ ሐምሌ 4/2017(ኢዜአ)፡- በሰሜን ወሎ ዞን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ16 ሺህ በላይ የተለያዩ የታዳሽ ሃይል አማራጮችን በማቅረብ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የዞኑ ውሃና ኢነርጂ መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የአማራጭ ኢነርጂ ቡድን መሪ ወይዘሮ ትርሃስ እቋር ለኢዜአ እንደገለጹት በገጠር ተበታትኖ የሚኖረውን ማህበረሰብ በታዳሽ ሃይል ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው።
በበጀት ዓመቱ ከ16 ሺህ በላይ የታዳሽ ሃይል አማራጮችን በማቅረብ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
ከቀረቡት የሃይል አማራጮች ውስጥም 12 ሺህ 187 የተሻሻሉ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎች፣ 3 ሺህ 764 የሶላር ቁሳቁሶችና 112 የባዮ ጋዝ ግንባታ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በቀረቡት የሃይል አማራጮችም 16 ሺህ 63 እማና አባዎራዎችን ከነሙሉ ቤተሰቦቻቸው ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።
የሃይል አማራጮቹን ማቅረብ የተቻለውም ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች በተገኘ ከ15 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪና በህብረተሰቡ ተሳትፎ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በመቄት ወረዳ የ017 ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር አስረሴ ቦጋለ እንደገለጹት ከባለሙያዎች በተሰጣቸው ምክር በመታገዝ የባዮ ጋዝ ግንባታ በማካሄድ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዚህም የምግብ ማብሰል፣ የመብራት አገልግሎት፣ ከባዮ ጋዝ ተረፈ ምርቱ የተፈጥሮ ማዳበሪያና ሌሎች ጥቅሞችን ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
"የተሻሻለ ፈጣን የምድጃ ተጠቃሚ በመሆናቸው ከኩበትና ከእንጨት ጪስ ስቃይ መገላገላቸውን የገለጹት ደግሞ በዞኑ የላስታ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ እታለም ጎሹ ናቸው። "
በማገዶ ፍለጋ ብዙ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን ያባክኑ እንደነበር ጠቁመው አሁን ላይ ጤናቸውን በጠበቀና ወጪን በቀነሰ መልኩ ምግብ አብስለው ቤተሰባቸውን እየመገቡ መሆኑን ተናግረዋል።