በመዲናዋ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ 15 ሺህ 960 ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት በቅተዋል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2017(ኢዜአ) ፡- በመዲናዋ በተጠናቀቀው የ2017 በጀት ዓመት 15 ሺህ 960 ፕሮጀክቶች በመንግሥትና በህብረተሰብ ተሳትፎ ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

3ኛው የአዲስ አበባ ምክር ቤት 4ኛ አመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ መካሄድ ጀምሯል። 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።

በሪፖርታቸውም በ2017 በጀት ዓመት የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በርካታ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

 ከእነዚህም መካከል የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል፣ የገበያ ማዕከላት፣ የጤና የትምህርት የኪነጥበብ እና ሌሎችም መሰረተ ልማቶች ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።

የአቅመ ደካማ ቤቶችን መገንባት እና ማደስ በበጎ ፈቃደኞች ብቻ የተሰራው 8 ሺህ 786 ቤቶች ሲሆን በከተማ አስተዳደሩ በጀት የተገነቡ መኖሪያ ቤቶች ደግሞ 5 ሺህ 176 መኖሪያ ቤቶች ናቸው ብለዋል።

በኮሪደር ልማቱም በካዛንችስ፣ ቦሌ፣ ልደታ፣ ላፍቶ፣ አራት ኪሎ እና ሌሎችም በግልና በመንግስት ተሳትፎ  5 ሺህ 563 ሱቆች መጠናቀቃቸውን ያነሱት ከንቲባዋ፥ 1 ሺህ 64 መስሪያ ሼዶችም ወደ አገልግሎት ገብተዋል ነው ያሉት።

በቀዳማዊ ልጅነት ንቅናቄም አዲስ አበባ ህጻናትን ለማሳደግ ምቹ ከተማ እንድትሆን በተጀመሩ ተግባራት 1 ሺህ 155 የህጻናት መጫወቻዎች መገንባታቸውን ገልጸዋል።

ለወጣቶች ስፖርት ማዘውተሪያ 122 ሜዳዎች ተጠናቀው ወደ አገልግሎት መግባታቸውንም አብራርተዋል።

በበጀት ዓመቱ በመጀመሪያው ምዕራፍ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ 153 የመኪና ማቆሚያና ተርሚናሎች ተጠናቀው ወደ አገልግሎት መግባታቸውን ገልጸዋል።

ሌሎችም በርካታ የልማት ሥራዎችን ጨምሮ 15 ሺህ 960 ፕሮጀክቶች ተገንብተው ለአገለግሎት መብቃታቸውን በማንሳት ከእነዚህ ውስጥም 16ቱ ሜጋ ፕሮጀክቶች ናቸው ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ 9 ሺህ የሚሆኑት በህብረተሰብ ተሳትፎ እና በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሰሩ  መሆናቸውን አንስተዋል።

የከተማዋን የመንገድ ተደራሽነትና የትራፊክ ፍሰትን የሚያሻሽሉ ጥራት ያላቸው የመንገድ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት በተሰራው ስራም 1 ሺህ 392 ኪሎ ሜትር የአስፋልት፣ የኮብል፣ የጠጠር፣ እና የእግረኛ መንገዶች ግንባታና ጥገና መከናወኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም