መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያ የምታስተናግደውን ሁለተኛ የተመድ የስርዓተ ምግብ ጉባኤ በሚገባ ማስተዋወቅ አለባቸው- ማንደፍሮ ንጉሴ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያ የምታስተናግደውን ሁለተኛ የተመድ የስርዓተ ምግብ ጉባኤ በሚገባ ማስተዋወቅ አለባቸው- ማንደፍሮ ንጉሴ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2017(ኢዜአ)፦ መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያ የምታስተናግደውን ሁለተኛ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስርዓተ ምግብ ጉባኤ አስቀድመው ማስተዋወቅ እንደሚገባቸው የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ(ዶ/ር) አስገነዘቡ።
ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስርዓተ ምግብ ጉባኤ ከሐምሌ 20 እስከ 22 ቀን 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ እና ጣልያን የጋራ አዘጋጅነት ይካሄዳል።
በጉባኤው ላይ የ160 ሀገራት ተወካዮች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽን ኢንቨስትመንት እና ፋይናንስ፣ የምግብ ስርዓት ሽግግር ሁለንተናዊነት እና የተገቡ ቃሎችን ከመፈጸም አንጻር ያለውን የተጠያቂነት ስርዓት ማጠናከር ጉባኤው ትኩረት የሚያደርግባቸው ሀሳቦች ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢኒስቲትዩት “ከራዕይ ወደ ተግባር: የኢትዮጵያ ዘላቂና አካታች የምግብ ስርዓት ሽግግር ጉዞ” በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጁት የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ(ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወንዳለ ሀብታሙ፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ(ዶ/ር) የምግብ ዋስትና በግለሰብ፣ በማህበረሰብ እና በሀገር ደረጃ ማረጋገጥ ወሳኝ ነው ብለዋል።
እንደ ሀገር የተያዘው ዋነኛ ግብ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ መሆኑንም ጨምረው አመልክተዋል።
የምግብ ሉዓላዊነት የምግብ አመራረታችንን በኛ ቁጥጥር ስር የማድረግ እና ዜጎችን በሌሎች ላይ ጥገኛ ሳንሆን በራሳችን መመገብ መቻል እንደሆነ ተናግረዋል።
የምግብ ስርዓት ሽግግር የምግብ ሉዓላዊትን የያዘ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው መንግስት በጉዳዩ ላይ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
በምግብ ስርዓት ሽግግር ከምርት እስከ ተጠቃሚ ባለው ሰንሰለት ውስጥ ሁሉን አቀፍ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለምግብ ስርዓት ሽግግር የአሰራር ማዕቀፎች በማዘጋጀት በመተግበሯ ውጤቶች ማስገኘታቸውን ጠቅሰዋል።
ጤናማ ምግብ ለሁሉም ዜጎች ግብ ያለው የምግብ ስርዓት ሽግግር ላይ አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ነው ያነሱት።
ኢትዮጵያ በምግብ ስርዓት ሽግግር ያላትን ተሞክሮዎች በዓለም መድረኮች እያቀረበች እንደምትገኝም ገልጸዋል።
ሁለተኛው የተመድ የስርዓተ ምግብ ጉባኤ በኢትዮጵያ መካሄዱ ሀገሪቱ ለምግብ ስርዓት ሽግግር ላከናወችው ስራ እውቅና የሰጠ ነው ብለዋል።
መገናኛ ብዙሃንም ኢትዮጵያ የምታስተናግደውን ሁለተኛ የተመድ የስርዓተ ምግብ ጉባኤ አስቀድመው እንዲያስተዋውቁ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ የኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው ብለዋል።
እንደ ሀገር ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ አምርቶ ራስን በመቻል አልፎም ለሌላው በመትረፍ የምግብ ሉዓላዊነትን በሁለንተናዊ ሁኔታ ማረጋገጥ ያለው ሚና ወሳኝ መሆኑንም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ግብርናን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ትላልቅ የፓናል ውይይቶችን እያዘጋጀ መሆኑን አመልክተው የዛሬው ውይይትም ሀገራዊ ተልዕኮውን የመወጣት አካል ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በስርዓተ ምግብ ትራንስፎርሜሽን፣ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ እና በግብርናው ዘርፍ ባደረገቻቸው ሀገር በቀል ሪፎርሞች ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች ጉባኤውን እንድታስተናግድ ለመመረጥ ምክንያቶች ናቸው።
ኢትዮጵያ በስርዓተ ምግብ ለውጥ ውስጥ እየተወጣች ያለው የመሪነት ሚና እና በማደግ ላይ ከሚገኙ ሀገራት በስርዓተ ምግብ ተምሳሌት የሆነች ሀገር መሆኗ ተመድ ዓለም አቀፉን ከፍተኛ ጉባኤ በኢትዮጵያ እንዲያደርግ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል።
በጉባኤው ኢትዮጵያ የስርዓተ ምግብ ሽግግርን ለማሳካት እያከናወነች ባለው ተግባር ዙሪያ ተሞክሮዋን ለዓለም ማህበረሰብ የማካፈል ስራ ታከናውናለች።