በአዲስ አበባ የሚካሄደው የተመድ የስርዓተ ምግብ ጉባኤ ኢትዮጵያ በምግብ ስርዓት ላከናወነችው ሥራ እውቅና የሚሰጥ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2017(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ የሚካሄደው የተመድ የስርዓተ ምግብ ጉባኤ ኢትዮጵያ በምግብ ስርዓት ላከናወነችው ሥራ እውቅና የሚሰጥ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍሬው ተገኝ(ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር "ከራዕይ ወደ ተግባር፤ የኢትዮጵያ ዘላቂና አካታች የምግብ ስርዓት ሽግግር ጉዞ" በሚል መሪ ሐሳብ ዐበይት ትኩረቱን በኢትዮጵያ ሥርዓተ ምግብ ላይ ያደረገ ውይይት በማካሄድ ላይ ይገኛል።


 

በዚሁ ወቅት የመነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍሬው ተገኝ(ዶ/ር) እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ለዘላቂ የልማት ግቦች ስኬት የበኩሏን አስተዋጽኦ እያደረገች ትገኛለች።

ኢትዮጵያ የምግብ ስርዓት ሽግግር ትግበራን በመጀመር ግንባር ቀደም ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።

በዚህም የተለያዩ የልማት ኢኒሼቲቮች መተግበራቸውን ጠቁመው፤ የሌማት ትሩፋት፣ የስንዴ ልማት፣ የአረንጓዴ አሻራ እና ሌሎችን ለአብነት አንስተዋል።

2ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስርዓተ ምግብ ጉባኤ ከሐምሌ 20 እስከ 22 ቀን 2017 በአዲስ አበባ በኢትዮጵያ እና በጣሊያን አስተናጋጅነት እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

ጉባዔው በኢትዮጵያ መካሄዱ ለሀገር ገጽታ ግንባታ ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን ገልጸው፤ በተለይም ኢትዮጵያ ለጀመረችው የምግብ ስርዓት ሽግግር ጉዞ እውቅና የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በተለይም ከለውጡ ወዲህ የምግብ ስርዓት ሽግግርን የሚያፋጥኑ የተለያዩ ብሔራዊ ፕሮግራሞችን በመቅረጽ በትኩረት እየሰራች እንደምትገኝ ይታወቃል።

ለአብነትም የሌማት ትሩፋት፣ የስንዴ ልማት፣ አረንጓዴ አሻራ፣ የትምህርት ቤት ምገባ፣ ኢትዮጵያ ታምርት እንዲሁም የሰቆጣ ቃል-ኪዳን ኢንሼቲቮች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብ ስርዓት ጉባዔን በስኬት ለማስተናገድ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም