ደምና የዓይን ብሌንን በመለገስ የሰዎችን ህይወት ከመታደግ ባለፈ ፍቅርና ወንድማማችነትን ማጎልበት ይገባል

ወላይታ ሶዶ፤ ሐምሌ 3/2017(ኢዜአ)፦ ደም እና የዓይን ብሌንን በመለገስ የሰውን ህይወት ከመታደግ ባለፈ ፍቅርና ወንድማማችነትን ለማጎልበት መስራት እንደሚገባ ተገለጸ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ 21ኛውን ዓለም አቀፍ የደም ለጋሾ ቀንን በማስመልከት ለበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾችና ተቋማት የምስጋና እና የእውቅና መርሃ ግብር አካሂዷል።

በመድረኩ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የወላይታ ሶዶ ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ተፈሪ አባተ በክልሉ የደም አቅርቦቱን ለማሳደግ እየተሰራ ነው።


 

በተለያዩ ምክንያቶች ደም የሚያስፈልጋቸውን ወገኖች ለመታደግ የተጀመረው ደም የማሰባሰብ ሥራ አበረታች ውጤት እየተገኘበት መሆኑን ጠቁመዋል።

የደም እና የዓይን ብሌን ልገሳ ውድ ስጦታ መሆናቸውን ገልጸው፣ ለጋሾችም የህይወት ዘመን አምባሳደሮች በመሆናቸው ክብር ይገባቸዋል ብለዋል።

ከክልሉ ህዝብ ቁጥር ጋር ሲታይ ከህብረተሰቡ የሚሰበሰበው ደም በቂ እንዳልሆነ ጠቁመው በቀጣይ የደም ለጋሾችን ቁጥር ለማሳደግ በቅንጅት የሚደረገው ጥረት ይጠናከራል ነው ያሉት።


 

የኢትዮጵያ የደም እና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ወይዘሮ ጤናዬ ደምሴ በበኩላቸው የደም ልገሳ መርሃ ግብር የደም ለጋሾችን ቁጥር እያሳደገ ቢመጣም ከሚያስፈልው ደም አንፃር በቂ ስላልሆነ አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ብለዋል።

በደም ህዋስ የሰዎችን ህይወት ከመታደግ በተጨማሪ መድኃኒት ለማምረት የ5 ዓመት ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም ምክትል ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል።

ይህም ከውጭ ሀገር በውድ ዋጋ የሚገባን መድኃኒት በሀገር ውስጥ ለማግኘት ከማስቻሉ ባለፈ የውጭ ምንዛሬን እንደሚያስቀርም አስረድተዋል።

በሀገር ውስጥ ለሚገኙ 55 የደም ባንኮች አስፈላጊው ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው

ህብረተሰቡም ደም መለገስን ባህሉ በማድረግ የሌሎችን ህይወት መታደግና የህይወት ግዴታውን መወጣት ይኖርበታል ብለዋል።

መድረኩ ለበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾችና ተቋማት ምስጋናና እውቅና ከመስጠት ባለፈ አዳዲስ ደም ለጋሾችን የማፍራት ዓላማ እንዳለው ተመላክቷል።

በመርሃ ግብሩ ከክልል አስከ ዞን ያሉ አመራሮች፣ በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች፣ የተቋማት ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም