የክልሉ መንግስት የጤና አገልግሎት ለሕብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ ተጠቃሚነቱን የሚያጎለብት ተግባር እያከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉ መንግስት የጤና አገልግሎት ለሕብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ ተጠቃሚነቱን የሚያጎለብት ተግባር እያከናወነ ነው

ቦንጋ ፤ ሐምሌ 3/2017 (ኢዜአ)፡- የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት የጤና አገልግሎት ለሕብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ ተጠቃሚነቱን ይበልጥ የሚያጎለብት ተግባር እያከናወነ መሆኑ ተገለጸ።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) በካፋ ዞን የተገነባውን የቆንዳ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።
በተጨማሪም በካፋ ዞን ሳይለም ወረዳ ከ78 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው የያዶታ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅና የያዶታ ጤና ጣቢያ ቀዶ ጥገና ማዕከልንም መርቀዋል ።
በዚህ ወቅት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት፤ የክልሉ መንግስት የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የሚያሳድጉ በርካታ ተግባራት እያከናወነ ነው ።
በተለይም ከማህበራዊ ዘርፍ ውስጥ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትንና ጥራቱን ለማሻሻል በተወሰደው እርምጃ የዛሬውን ጨምሮ ባለፉት የለውጥ ዓመታት አራት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ተመርቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ተደርጓል ብለዋል።
በተጨማሪም በርካታ የማስፋፊያና በግብአት የማሟላት ስራም መከናወኑን አንስተዋል።
ዛሬ የተመረቀው የቆንዳ ሆስፒታል ለወረዳውና ለአጎራባች አካባቢዎች ነዋሪዎች አገልግሎት የሚሰጥ ነው ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ፤ የክልሉ መንግስት የጤና አገልግሎት ለሕብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ ተጠቃሚነቱን ይበልጥ የማጎልበት ተግባር እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም በበኩላቸው፤ የቆንዳ የመጀመሪያ ሆስፒታል በክልሉ መንግስት 120 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መገንባቱን ገልጸዋል።
የሆስፒታሉ መገንባት ሕብረተሰቡ የተሻለ የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።
ዛሬ የተመረቀው የቆንዳ ሆስፒታል በሕብረተሰቡ ሲነሳ ለቆየው ጥያቄ መልስ የሰጠ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ ናቸው ።
በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደርና የግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ ማስረሻ በላቸውን ጨምሮ ሌሎችም ከፍተኛ አመራሮችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።