ሀገራዊ የብልጽግና ጉዞ እንዲሳካ ወጣቶች የሚያደርጉትን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ድጋፍ ማጠናከር አለባቸው

አርባ ምንጭ ፤ ሐምሌ 3/2017(ኢዜአ)፦ሀገራዊ የብልጽግና ጉዞ እንዲሳካ ወጣቶች አቅማቸውን በማስተባበር የሚያደርጉትን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ድጋፍ ማጠናከር እንዳለባቸው የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

 የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የወጣቶች ምክር ቤት ምስረታ ዛሬ በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ወይዘሮ የሺወርቅ አያና እንደገለጹት ወጣቶች ባለራዕይ በመሆን ባላቸው እውቀትና ክህሎት ለሀገር የብልጽግና ጉዞ መሳካት የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል።


 

ለሀገር ሰላምና ልማት መጠናከር የወጣቶች የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፣ መንግስት ለወጣቱ የሰጠውን ልዩ ትኩረት በመጠቀም በሁሉም የልማት መስኮች የሚያደርጉትን ተሳትፎና ያላቸውን ተጠቃሚነት ሊያሳድጉ ይገባል ብለዋል።

መንግስት የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሲያከናውናቸው የነበሩ ተግባራትን በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ወይዘሮ የሺወርቅ ጠቁመዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትልና የወጣቶች ዘርፍ ሃላፊ አቶ ማርቆስ ማቴዎስ በበኩላቸው እንዳሉት ቢሮው የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ ይገኛል።

የክልሉ የወጣቶች ምክር ቤት አስፈጻሚ አካላት ምርጫ ብዝሃነትን መሠረት ያደረገ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ መሆኑንም ገልጸዋል።


 

ተመራጮች የክልሉን ወጣቶች ወክለው በተለያዩ መድረኮች እንደሚሳተፉ ገልጸው፣ በቀጣይ እንቅስቃሴያቸው ምክንያታዊ በመሆን ለወጣቶች ሁለንተናዊ ድምፅ ሊሆኑ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

የክልሉ ብሎም የሀገሪቱ እድገትና ሰላም በዘላቂነት ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ወጣቶች የበኩላቸውን እንዲወጡ አቶ ማርቆስ ጥሪ አቅርበዋል።

የክልሉ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሆኖ የተመረጠው ወጣት ቲቶ ሐኩቴ በበኩሉ፣ በቀጣይ የወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲጎለብትና የወጣቱ ጥያቄዎች በሂደት እንዲመለሱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እንደሚሰራ ተናግሯል።


 

የክልሉ ወጣቶች ያላቸውን እውቀትና ጉልበት አቀናጅተው ለክልሉና ለሀገር ልማት በማዋል የበኩላቸውን እንዲወጡም አስገንዝቧል።

ዛሬ በተካሄደው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የወጣቶች ምክር ቤት ምስረታ ላይ  በሥራ አስፈጻሚነት የተመረጡ 15 ወጣቶችም ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም