በጌዴኦ ዞን የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በትብብር እየተሰራ ነው - የዞኑ አስተዳደር - ኢዜአ አማርኛ
በጌዴኦ ዞን የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በትብብር እየተሰራ ነው - የዞኑ አስተዳደር

ዲላ፤ ሐምሌ 4/2017(ኢዜአ)፦ በጌዴኦ ዞን የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ከህብረተሰቡ እና ከአጋር አካላት ጋር በትብብር የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።
በዞኑ ዲላ ከተማ አስተዳደር በ40 ሚሊዮን ብር ወጪ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ እየተከናወነ ነው።
ግንባታው የዞኑ አስተዳደር ከዓለም አቀፉ የትምህርትና ባህል ተራድኦ ድርጅት(WECA) ጋር በመተባበር የሚከናወን ሲሆን ግንባታውን በተያዘው ዓመት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚደረግ ተመላክቷል።
የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ(ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት በዞኑ የትምህርት ስብራትን በዘላቂነት ለመቅረፍና ጥራትን ለማስጠበቅ ከህብረተሰቡ እና ከአጋር ድርጅቶች ጋር በትብብር እየተሰራ ነው።
በተለይ በተያዘው በጀት ዓመት በዞኑ 80 በመቶ የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ያሉባቸውን የመሰረተ ልማት ችግር በማሻሻል የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ትኩረት እንደሚደረግ ገልጸዋል።
የትምህርት ቤቱ ግንባታ በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ ክትትል የሚደረግ መሆኑን አንስተው የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ሞዴል ትምህርት ቤት ከመፍጠር ባለፈ ደረጃውን ወደ አዳሪ ትምህርት ቤት ለማሳደግ መታቀዱንም ገልጸዋል።
ትምህርት ቤት የእውቀት መገበያያ ብቻ ሳይሆን የትውልዱ የስብዕና ግንባታ ማዕከል መሆኑን ያነሱት ደግሞ የዓለም አቀፉ የትምህርትና ባህል ተራድኦ ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ ባንግ ቱንጋዋን ናቸው።
ድርጅታቸው በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የትምህርት መሰረተ ልማትን በማስፋፋት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት እያገዘ ነው ብለዋል።
በዲላ ከተማ ከዞኑ አስተዳደር ጋር በመተባበር የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከመገንባት ባሻገር በትምህርት ቤቱ የውጭ ቋንቋዎችን በማስተማር የትምህርት ስርዓቱን እየደገፈ መሆኑን ጠቁመዋል።
የጌዴኦ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ዘማች ክፍሌ በበኩላቸው የትምህርት ቤቱን የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ በተያዘው ዓመት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ይህም 13 መማሪያ ክፍሎችን ጨምሮ የአስተዳደርና የመጸዳጃ ህንጻዎችን እንዲሁም የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ያካተተ ሲሆን ለዚህም ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚደረግ ገልፀዋል።
በአሁኑ ወቅትም አራት የመጀመሪያ ደረጃ የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ መጠናቀቃቸውን አመልክተዋል።