ኢትዮጵያ በስደተኞች አያያዝ አርዓያነት ያለው ተግባር እያከናወነች ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በስደተኞች አያያዝ አርዓያነት ያለውና የሚደነቅ ተግባር እያከናወነች ነው ሲሉ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ረዳት ተጠሪ ዴቪድ ካርፕ ገለጹ፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከሃያ ስድስት አገራት በተለያየ ምክንያት የመጡ ከ1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞች እና  ጥገኝነት ጠያቂዎችን በመቀበል ተገቢውን ጥበቃና ከለላ እየሰጠች ትገኛለች።

በኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ረዳት ተጠሪ ዴቪድ ካርፕ፥  ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የስደተኞች አያያዝ መርህን ባከበረ መልኩ ለስደተኞች አገልግሎት እየሰጠች እንደምትገኝ  ለኢዜአ ገልጸዋል።

ስደተኞች ባሉባቸው አካባቢዎች የመንገድ፣ የውሃ፣ የመብራት፣ የትምህርት፣ የጤና እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ተገንብተው አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ስደተኞች  ከተቀባዩ የህብረተሰብ ክፍል ጋር በማስተሳሰር በስራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑንም እንዲሁ፡፡

ይህም ኢትዮጵያን ለስደተኞች ከፍተኛ ትኩረት ከሚያደርጉ እና ክብር ከሚሰጡ የዓለም ሀገራት መካከል አንዷ እንደሚያደርጋት አንስተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በስደተኞች አያያዝ ዙሪያ እያከናወነቻቸው ያሉ ተግባራት ለሌሎች የዓለም አገራት አርዓያ እንደሚሆኑም ጠቁመዋል፡፡

ረዳት ተጠሪው አክለውም የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ለዚህ ተግባራቸው ምስጋና ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡

በቀጣይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን በስደተኞች አያያዝ ላይ ያለውን ቅንጅታዊ ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም