በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ224 ሚሊዮን ብር በላይ ከምዝበራ ማዳን ተችሏል

ቦንጋ ፤ ሐምሌ 4/2017(ኢዜአ) ፡- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተከናወነ ሙስናን የመከላከል ስራ ከ224 ሚሊዮን ብር በላይ የመንግሥትና የህዝብ ሃብት ከምዝበራ ማዳንና ማስመለስ መቻሉን የክልሉ ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ገለጸ።

በበጀት ዓመቱ በክልሉ 4 ሺህ 200 የመንግስት ሰራተኞችን በመመዝገብ የምስክር ወረቀት መሰጠቱም ተገልጿል።

የክልሉ ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሉሰው ዘውዴ ለኢዜአ እንደገለፁት፣ በተገባደደው በጀት ዓመት በትውልድ ስነ-ምግባር ግንባታና የአስቸኳይ ሙስና መከላከል ስራ ትኩረት ተደርጎ ሲሰራ ቆይቷል።

እንዲሁም በአሰራር ስርዓት ጥናትና በሙስና መረጃ ማደራጀትና መተንተን እንዲሁም በተቋም ግንባታ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።

በዓመቱ 729 ጥቆማዎችን በጽሁፍ፣ በስልክ፣ በአካልና በተለያዩ የመረጃ መቀበያ አማራጮች መቀበሉን ጠቁመዋል።

ጥቆማዎቹም በሀሰተኛ ሰነድ መጠቀም፣ በሰነድ ማጭበርበር፣ በሀብት ምዝበራ፣ ስልጣንን ያለ አግባብ መጠቀም፣ ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ማፍራትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ እንደነበሩም ኮሚሽነር ሙሉሰው ገልፀዋል።

ከቀረቡት ጥቆማዎች ውስጥ 292ቱ በአስቸኳይ ሙስና መከላከል እንዲሁም 124ቱ ላይ ማስረጃን በማደራጀትና በመተንተን  ለፍትሕ አካላት የማስተላለፍ ስራ ተሰርቷል ብለዋል።

ኮሚሽነሩ አያይዘውም 202 ጥቆማዎች በአስተዳደራዊ እርምጃ ምላሽ የተሰጠ ሲሆን ቀሪ 27 የምክርና የህግ ከለላ መስጠት ተችሏል ነው ያሉት።

292 ጥቆማዎች ላይ በተሰራው አስቸኳይ የሙስና መከላከል ስራ ሊመዘበር የነበረን ከ178 ሚሊዮን 871 ሺህ ብር በላይ ማዳን መቻሉን ኮሚሽነር ሙሉሰው ተናግረዋል።

እንደ ኮሚሽነር ሙሉሰው ገለጻ ከገንዘብ በተጨማሪ ከ166 ሺህ 708 ካሬ የከተማ እንዲሁም ከ505 ሄክታር በላይ የገጠር መሬት ማዳን ተችሏል።

በኦዲት ግኝት ተመዝብሮ የነበረን ሀብት ለማስመለስ በተደረገው ጥረትም ከ45 ሚሊዮን 618 ሺህ ብር በላይ እንዲሁም በዓይነት የተለያዩ የመንግስት ንብረትና ቁሳቁሶችን የማስመለስ ስራ መሰራቱን ገልፀዋል።

ይህም በአጠቃላይ በተሰራው ሙስናን የመከላከል ስራ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ224 ሚሊዮን 489 ሺህ ብር በላይ በገንዘብና በዓይነት የመንግሥትና የህዝብ ሃብትን ከምዝበራ ማዳንና ማስመለስ መቻሉን ነው የገለጹት።

በተጨማሪም በተገባደደው በጀት ዓመት 4 ሺህ 200 የመንግስት ሰራተኞችን በመመዝገብ የምስክር ወረቀት መሰጠቱን ጠቁመው የመረጃውን ትክክለኛነት በማረጋገጥ ግልፀኝነትና ተጠያቂነትን የማስፈን ስራ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኮሚሽኑን የአሰራር ስርዓት ከማሻሻልና ብቃት ከማሳደግ አኳያ በተሰሩ ስራዎች ሶስት የተለያዩ ሕጎችን በማዘጋጀት ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉን ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።

በአዲሱ በጀት ዓመትም ተግባራቱን ይበልጥ አጠናክሮ በማስቀጠል የተመዘገቡ ሀብቶችን ትክክለኛነት ማጣራትና የሀብት ምዝገባን በቴክኖሎጂ የማስደገፍ ስራ በትኩረት ይሰራል ብለዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም