ፖለቲካ
የጋምቤላ ህዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት 6ኛ መደበኛ ጉባዔ ከነገ ጀምሮ ይካሄዳል
Jul 24, 2024 75
ጋምቤላ ፤ ሐምሌ 17/2016 (ኢዜአ)፡- የጋምቤላ ህዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት 6ኛ የስራ ዘመን 3ኛ ዓመት 6ኛ መደበኛ ጉባዔ ከነገ ጀምሮ እንደሚካሄድ የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ባንቻየሁ ድንገታ ገለጹ። ወይዘሮ ባንቻየሁ ጉባዔውን አስመልክተው ዛሬ እንደገለጹት የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ የሥራ ዘመን 3ኛ ዓመት 6ኛ መደበኛ ጉባዔ ከነገ ሐምሌ 18 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በጋምቤላ ከተማ ይካሄደል። ጉባዔው በሚኖረው የሶስት ቀናት ቆይታ የክልሉን የ2016 በጀት ዓመት የልማትና መልካም አስተዳደር እቅድ አፈጻጸም እንዲሁም የጠቅላይ ፍርድ ቤትና የዋና ኦዲት መስሪያ ቤት የስራ ክንውን ሪፖርት አድምጦ እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል ብለዋል። እንዲሁም የክልሉን የ2017 በጀት ዓመት የልማትና መልካም አስተዳደር እቅድ፣ የማስፈፀሚያ በጀትና ሌሎች ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ ገልጸዋል። በጉባዔው መጨረሻም የጉባዔው አባላትና ተሳታፊዎች የችግኝ ተከላ እንደሚያካሄዱ አፈ ጉባዔዋ ተናግረዋል። በጉባዔው ላይ የምክር ቤቱ አባላትን ጨምሮ ከ350 በላይ የክልል፣ የዞንና የወረዳ የአመራር አካላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች ተጋበዥ እንግዶች ይሳተፋሉ ብለዋል።    
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ የተለያዩ አዋጆችን በማፅደቅ ተጠናቀቀ
Jul 23, 2024 118
ታርጫ፤ ሐምሌ /2016 (ኢዜአ)፦ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ስድስተኛ መደበኛ ጉባኤ የተለያዩ አዋጆችን በሙሉ ድምጽ በማጽደቅ ተጠናቀቀ። ምክር ቤቱ በዋና አፈ ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ የቀረቡትን ወይዘሮ አምሳለ ንጋቱ የምክር ቤቱ የህግ፣ የፍትህና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አድርጎ መሾሙም ተገልጿል። በመቀጠልም ምክር ቤቱ በክልሉ መንግሥት የቀረቡ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ አፅድቋል።   አፈ ጉባዔ ወንድሙ የአዋጆቹን ዓላማና አስፈላጊነትና እንዲሁም ዝርዝር ይዘትና የተፈጻሚነት ወሰን ለምክር ቤቱ አባላት ማብራሪያ ሰጥተዋል። በምክር ቤቱ ውሳኔ የፀደቁ አዋጆች የክልሉን ሁለንተናዊ ዕድገት በማፋጠን የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የጎላ ድርሻ እንዳላቸውም አፈ ጉባኤው አስረድተዋል። ምክር ቤቱ በታርጫ ከተማ ለሁለት ቀናት ሲያካሄድ የቆየውን መደበኛ ጉባኤንም በዛሬው ዕለት አጠናቋል።  
የፓርቲውን የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም ለማሳደግ መጠነ ሰፊ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ተሰጥተዋል-ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ
Jul 23, 2024 184
አዳማ ፤ሐምሌ 16/2016(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የብልጽግና ፓርቲን የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም ለማሳደግ መጠነ ሰፊ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች መሰጠታቸውን በፓርቲው የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ሀላፊ (ዶ/ር) ቢቂላ ሁሪሳ ገለጹ። በክልሉ ከሦስት ሚሊዮን በላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት ስልጠና መሰጠቱም ተገልጿል። የኦሮሚያ ክልል የተጠናቀቀው በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የተያዘው በጀት ዓመት እቅድ ላይ ያተኮረ ውይይት በአዳማ አባገዳ አደራሽ እየተካሄደ ነው። በግምገማው ላይ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ሰዓዳ አብዱራህማን፣ በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ እንዲሁም የክልሉ ከፍተኛ አመራር አባላት፣ የዞን፣ የከተሞችና የወረዳ አመራር አባላት ተገኝተዋል። በዚሁ ወቅት የፓርቲውን የእቅድ አፈጻጸም ያቀረቡት በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ሀላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ፓርቲው በበጀት ዓመቱ የተለያዩ ተግባራት ማከናወኑን ገልጸዋል።   ፓርቲው የአመራርና የአባላት አቅምን ለማጠናከር በተለያዩ ጊዜያት በአገራዊ አጀንዳዎች ላይ ያተኮሩ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች መስጠቱን ተናግረዋል። በዚህም መምህራን፣ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮችን ጭምር ተደራሽ ያደረገ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ አቅም ግንባታ ስልጠና መሰጠቱን አስረድተዋል። በአቅም ግንባታ ስልጠናዎቹ ላይ በአጠቃላይ በክልሉ ከሦስት ሚሊዮን በላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት ስልጠና መሰጠቱን ነው የተናገሩት። በሌላ በኩል የአገራዊ ምክክር ሂደቱ እንዲሳካም በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ከስቪክ ማህበራት ጋር የተሻለ ግኑኝነት የተፈጠረበት ዓመት መሆኑንም አንስተዋል። በተጨማሪም በጋራ ብልፅግና ትርክት ላይ አመራሩና አባሉ የጋራ ግንዛቤና አረዳድ እንዲኖራቸው ማድረግ ተችሏል ብለዋል።    
የክልሉን ሠላም በዘላቂነት ለማስቀጠል ህብረተሰቡ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል- የሠላም ካውንስሉ
Jul 23, 2024 178
ባህር ዳር፤ ሐምሌ 16/2016(ኢዜአ)፡- የአማራ ክልልን ሠላም በዘላቂነት ለማስቀጠል እየተደረገ ያለውን ጥረት በመደገፍ ህብረተሰቡ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ የክልሉ የሠላም ካውንስል ገለጸ። በባህር ዳር ከተማ አስተዳደርና በሰሜን ጎጃም ዞን የተመረጡ የሠላም ካውንስል አባላት "ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም" በሚል መሪ ሃሳብ የሠላም ውይይት እያካሄዱ ነው። የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል ሰብሳቢ አቶ ያየህራድ በለጠ በውይይቱ ላይ እንዳመለከቱት፤ በክልሉ ሠላም እንዲረጋገጥ ካውንስሉ የማመቻቸት ስራ በማከናወን ላይ ይገኛል። ይህም ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር መሆኑን ተናግረዋል። በተለይ ችግር ውስጥ የገቡ ወገኖች ችግሩን በውይይትና በንግግር መፍታት እንደሚገባ ተገንዝበው ይህንን መልካም ዕድል መጠቀም እንዳለባቸው አመልክተዋል። ችግሮችን በውይይት በመፍታታ የክልሉን ሠላም በዘላቂነት ለማስቀጠል እየተደረገ ያለውን ጥረት በመደገፍ ህብረተሰቡ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም ገልጸዋል። በውይይቱ ላይ በባህር ዳር ከተማ አስተዳደርና በሰሜን ጎጃም ዞን የተቋቋሙ የሠላም ካውንስሉ አባላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
በአማራ ክልል የአማራ ፋኖ ሸዋ ዕዝ ዋና አዛዥ ኮሎኔል አሰግድ መኮንን ለመንግስት ፀጥታ ሃይሎች እጁን ሰጠ
Jul 22, 2024 574
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 15/ 2016 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል በርካታ የታጣቂ ቡድን አባላት እና አመራሮች በመንግስት የቀረበላቸውን የሰላም አማራጭ ተቀብለው ሰላማዊ ሕይወት እየመሩ መሆኑን የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል አስታወቀ። የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መረጃ እንዳስታወቀው፤ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩትን የፀጥታ ችግሮች በንግግርና በዉይይት በመፍታት ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በመንግስት ለታጣቂ ቡድን አባላት እና አመራሮች በተደጋጋሚ የሰላም አማራጮች ሲቀርቡ ቆይተዋል፡፡ ይሁንና በክልሎችም ሆነ በፌደራል መንግስት እያቀረበ ያለው የሰላም አማራጭ እንዳይሳካ እና ወደ መሬት እንዳይወርድ በተለይም ደግሞ ውጭ ሆነው በትግሉ ስም ጥቅም የሚያግበሰብሱ አንዳንድ ጽንፈኛ የዲያስፖራ አባላት ሰብስበው በሚልኩት ረብጣ ዶላር እንዲሁም ንፁሃንን አግተውና በጭካኔ ገድለው በሚጠይቁት እና በሚዘርፉት ገንዘብ ጥቅም የሰከሩ አንዳንድ የታጣቂ ቡድን አባላትና አመራሮች የሰላሙን አማራጭ ሲገፉ መቆየታቸውን የጋራ ግብረ ሀይሉ መግለጫ አመልክቷል፡፡ መግለጫው አያይዞም፤ከጥቅም፣ከጎጠኝነት እና ከገንዘብ ክፍፍል ጋር በተያያዘ በአብዛኛው በታጣቂ ቡድኑ አባላት እና በቡድኑ አመራሮች መካከል በሚፈጠር አተካራ እና የእርስ በርስ መጠፋፋት የትግሉ ዓላማ ከመስመር ወጥቷል በሚል በራሳቸው በቡድኑ አባላት እና አመራሮችም ጭምር እየታየ እና እየተገለፀ መምጣቱ ክልሎችን ለግጭትና ለትርምስ እየዳረገ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ ይህን ተከትሎም ለመንግሰት እጃቸውን በመስጠት ወደ ሰላማዊ ህይወት እየተቀላቀሉ ያሉ የታጣቂ ቡድን አባላት እና አመራሮች ቁጥር ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልጿል፡፡ በዛሬው እለትም በአማራ ክልል የአማራ ፋኖ ሸዋ ዕዝ ዋና አዛዥ ኮሎኔል አሰግድ መኮንን ለመንግስት ፀጥታ ሃይሎች እጁን መስጠቱን የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል አስታውቋል፡፡ ግለሰቡ እጁን የሰጠው በፅንፈኛ ሃይሉ አመራሮች እና ታጣቂ ቡድን አባላት አማካኝነት በአማራ ክልል ህዝብ ላይ የሚፈፀሙ አሰቃቂ ግድያዎች፣ እገታዎች፣አስገድዶ መድፈሮች፣ ለሕዝብ ጠቀሜታ የሚውሉ መሰረት ልማቶች ውድመት፣ አፈና እና ሌሎችም ኢሰብአዊ ድርጊቶች እተበራከቱ በመምጣታቸው እንደሆን በሰጠው ቃል ማረጋገጡን መግለጫው ጠቁሟል፡፡ የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ሃይል አክሎም ኮሎኔል አሰግድ መኮንን እጁን የሰጠው ከቅርብ አጃቢው ገበየሁ ወንድማገኝ ከተባለ የቡድኑ አባል ጋር መሆኑን አስታውቋል፡፡ ወደ ሰላማዊ ህይወት ለመቀላቀላቸው ትግሉ በአማራ ክልል ህዝብ ስም ቢካሄድም የጠራ ጥያቄ የሌለውና ክልሉን ለምስቅልቅል እና ለልማት እጦት እያደረገ ያለ እንዲሁም በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት ባሉ የተለያዩ ሃይሎች ፍላጎት ማስፈፀሚያ በመጠለፉ ምክንያት እንደሆነ መግለፃቸውን መግለጫው ጠቁሟል፡፡ የጽንፈኛ ኃይሉን በሚመሩት በእስክንድር ነጋና በዘመነ ካሴ መካከል የተፈጠረው ሽኩቻ ህዝቡን የከፋ ዋጋ ከማስከፈል የዘለለ ወደ አንድ የሚመጣበት ዕድል ሊኖረው እንደማይችል መረዳቱንም ኮለኔል አሰግድ ገልጿል፡፡ በአማራ ክልል በተቀሰቀሰው ግጭት የክልሉ ህዝብ ለከፋ ማህበራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል መዳረጉን የገለፀው ኮለኔል አሰግድ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ሊፈቱ ይገባል የሚል አቋም እንዳለው ተናግሯል፡፡ ተሳስተውና ተደናግረው ቡድኑን የተቀላቀሉ የፅንፈኛ ቡድኑ አባላትና አመራሮች መንግስት ያቀረበውን የሰላም አማራጭ ተጠቅመው እጃቸውን እንዲሰጡም አሳስቧል፡፡ በመጨረሻም የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል የሰላምን አማራጭ በመግፋት አሁንም በትጥቅ ትግል በሚገፉ ሀይሎች ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን እየገለፀ፤ በዚህ አጋጣሚ የሰላም አማራጭን ተቀብለው ለሚመጡ የታጣቂ ቡድን አመራሮች እና አባላት ግብረ ሀይሉ የሚያደርገውን ድጋፍና እና ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ሃይል በመግለጫው አስታውቋል፡፡
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምሁራን ለአብሮነትና ለሰላም እሴት ግንባታ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ
Jul 22, 2024 182
ጂንካ ፤ ሐምሌ 15/2016 (ኢዜአ):-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ ምሁራን ለአብሮነትና ለሰላም እሴት ግንባታ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ የክልሉ የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ አለማየሁ ባውዲ አስገነዘቡ። የክልሉ መንግሥት ከተለያዩ ተቋማት ከተውጣጡ ምሁራን ጋር በሀገራዊ፣ ክልላዊ እና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ በአሪ ዞን ጂንካ ከተማ እየመከረ ነው።   አቶ አለማየሁ በመድረኩ ላይ እንዳስገነዘቡት ምሁራን አብሮነትን የሚያጠናክሩ የጋራ እሴቶችን በመገንባት የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን ማጎልበት ይጠበቅባቸዋል። በተለይ በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት በሚከናወኑ ሥራዎች ውስጥ ገንቢ ሚናቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል። የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ በበኩላቸው በዞኑ ሁለንተናዊ ልማትን ለማረጋገጥ የምሁራን ሚና ወሳኝ መሆኑን ነው የተናገሩት። በመሆኑም ምሁራን በሁሉም መስኮች ገንቢ ሀሳቦችን በማፍለቅና ችግር ፈቺ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በማመላከት ለአካባቢው ዘላቂ ሰላምና ልማት የሚያደርጉትን ተሳትፎ እንዲያጠናክሩ አሳስበዋል። ምሁራኑ በቅርቡ የተመሰረተውን የአሪ ዞንን የሰላምና የአብሮነት ማዕከል ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት በተለያየ መንገድ እንዲያግዙም ጠይቀዋል። በምክክር መድረኩ ላይ በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የሰላም ሚኒስቴር አማካሪ አቶ ካይዳኪ ገዛኸኝን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራር አካላት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እና ምሁራን ታድመዋል።    
የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ መመለስ የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል-ዶክተር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ
Jul 22, 2024 189
ቦንጋ ፤ ሐምሌ 15/2016 (ኢዜአ)፡- በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት አመት የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ መመለስ የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) አስታወቁ። የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 6ኛ መደበኛ ጉባኤ እየተካሄደ ነው። የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) የክልሉን መንግስት የ2016 በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል። ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳመለከቱት የክልሉ መንግሥት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ መመለስ የሚያስችሉ ተግባራትን አከናውኗል። በበጀት ዓመቱ በጀት በመመደብና ህብረተሰቡን በማሳተፍ ግቦችን ለማሳካት የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመው የሚመደበውን ውስን ሃብት በአግባቡ ለመጠቀምና ለማስተዳደር የሚያስችል ስራ መከናወኑንም አመልክተዋል። ወቅታዊ ክልላዊ ነባራዊ ሁኔታን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ከክልል ማዕከል ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችን የመገምገም፣ የማጥራትና የመተካካት ስራም መከናወኑን አንስተዋል። ከብልሹ አሠራር የጸዳ አመራር የመገንባት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዶክተር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ ተናግረዋል። የክልሉን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ በተሰራው ስራ ውጤት መገኘቱን ጠቁመው አሁን ላይ በክሉሉ ሁሉም አካባቢዎች ሰላም ማስፈን መቻሉን ገልፀዋል። በበጀት ዓመቱ ሙስናን ለመከላከል በተደረገ ጥረት ባክኖ የነበረና ሊባክን የነበረን ከ95 ሚሊዮን 32 ሺህ ብር በላይ ማስመለስና ማዳን መቻሉን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አመልክተዋል።   በተጨማሪም 1 ሺህ 927 ሄክታር የገጠርና 237 ሺህ 592 ካሬ የከተማ መሬት እንዲሁም የተለያዩ ሀብቶችን ማስመለስና ማዳን መቻሉንም ጠቅሰዋል። ከኢኮኖሚ ዘርፍ አንፃርም በግብርናው ልማት ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ የአመራረት ዘዴዎችን ተግባራዊ በማድረግ በመኸርና በበልግ በዋና ዋና ሰብሎች 688 ሺ ሄክታር መሬት በመሽፈን 19 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ የተቀናጀ የገቢ አሰባሰብና አስተዳደር ሥርዓትን በመከተል በበጀት ዓመቱ ከ5 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ላይ ገቢ በመሰብሰብ የእቅዱን ከ95 በመቶ በላይ መፈፀም መቻሉን አመልክተዋል ። በሁሉም መዋቅሮች በተደረገው ልዩ ድጋፍና ክትትል በበጀት ዓመቱ ለ64 ሺ ሰዎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉንም አንስተዋል፡፡ የክልሉን አቅም መሠረት በማድረግ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት በተደረገ ጥረት በበጀት ዓመቱ 16 ቢሊዮን ብር ያስመዘገቡ 41 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በግብርናና ኢንዱስትሪ ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉንም ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ አስታውቀዋል።      
የሴክተር መስሪያ ቤቶች ዕቅድ የመልካም አስተዳደር ችግርና ብልሹ አሰራርን የሚቀርፍ መሆን አለበት - አቶ እንዳሻው ጣሰው
Jul 22, 2024 187
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 15/2016(ኢዜአ)፦ የሴክተር መስሪያ ቤቶች ዕቅድ የመልካም አስተዳደር ችግርና ብልሹ አሰራርን የሚቀርፍ፣ የዋጋ ንረትን የሚያረጋጋ መሆን አለበት ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው ገለጹ። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት የሴክተር መስሪያ ቤቶች የ2017 በጀት አመት ዕቅድ እየገመገመ ይገኛል።   የሁሉም ሴክተር መስሪያ ቤቶች ዕቅድ የመልካም አስተዳደር ችግርና ብልሹ አሰራርን የሚቀርፍ፣ የዋጋ ንረትን የሚያረጋጋ፣ የክልሉን ምርታማነት የሚያሳድግ፣ ዘላቂ ሰላም የሚያረጋግጥ እና በሁሉም መስክ ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆን እንዳለበት ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል። የሴክተር መስሪያ ቤቶች የ2017 በጀት አመት ዕቅድ በጥልቀት ተገምግሞ ቀጣይ አቅጣጫ እንደሚቀመጥ ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በኦሊምፒክ ጨዋታዎች የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ዛሬ ወደ ፓሪስ ይሸኛል 
Jul 22, 2024 210
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 15/2016(ኢዜአ)፦በፓሪስ በሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ዛሬ በብሔራዊ ቤተ-መንግስት ሽኝት ይደረግለታል። በሽኝት መርሐ ግብሩ ላይ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ተሳታፊ ስፖርተኞችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከሐምሌ 19 እስከ ነሐሴ 5 ቀን 2016 ዓ.ም በፓሪስ ይካሄዳል። በውድድሩ ላይ ከ206 አገራት የተወጣጡ (በዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ጥላ ስር የሚወዳደሩ ገለልተኛ አትሌቶችና የኦሊምፒክ የስደተኞች ቡድን ጨምሮ) 10 ሺህ 714 ስፖርተኞች በ32 የስፖርት ዓይነቶች ይሳተፋሉ። ኢትዮጵያም በአትሌቲክስ፣ ውሃ ዋናና ቦክስ ስፖርቶች ትሳተፋለች።   የኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ልዑካን ቡድን ለኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከሚያዚያ ወር 2016 ዓ.ም አንስቶ ዝግጅቱን ሲያደርግ እንደቆየ ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በተያያዘ ዜና የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች የሚሳተፉ አትሌቶችን ዛሬ ማለዳ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ጎብኝተዋል። ሚኒስትሯ በዓለም አደባባይ ኢትዮጵያን የምታስጠሩ አትሌቶች በዘንድሮው ኦሊምፒክም በአሸናፊነትና በጀግንነት ታሪክ ሀገራችሁን እንደምታስጠሩ እምነቴ ነው ብለዋል። አትሌቶቹ የኢትዮጵያን ገጽታ በመገንባት ትልቅ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ በምትታወቅበት የቡድን ስራና ስፖርታዊ ጨዋነት ውጤት ለማምጣት እንዲሰሩ አሳስበዋል። በኦሊምፒክ የሚሳተፉ አትሌቶችም ስለ ቅድመ ዝግጅታቸውና ስላሉበት ወቅታዊ ሁኔታ በመግለፅ ከሚኒስትሯ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።      
ሰላማዊ አማራጭን በመከተል ለሚመለሱ አካላት የክልሉ መንግሥት በር አሁንም ክፍት ነው -አቶ ሽመልስ አብዲሳ
Jul 21, 2024 159
አዳማ ፤ ሐምሌ 14/2016(ኢዜአ)፦ ሰላማዊ አማራጭን በመከተልና በመምረጥ ለሚመለሱ አካላት የክልሉ መንግሥት በር አሁንም ክፍት ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ። የሰላም አማራጭን ወደ ጎን በመተው የጥፋት መንገድ የመረጡት አካላት ላይ የህግ የበላይነት የማረጋገጥ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። አቶ ሽመልስ አብዲሳ ለጨፌ ኦሮሚያ አባላት ባቀረቡት የበጀት ዓመቱ እቅድ አፈጻጸምና የቀጣይ በጀት ዓመት ላይ ያቀረቡትን ሪፖርት መሰረት በማድረግ ከአባላቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። በዚህም መሰረት በየደረጃው ያሉ የፀጥታ አካላት፣ ሰላም ወዳዱ ህዝብና መንግሥት በትብብር እያከናወኑ ባሉት ተግባር በክልሉ እየሰፈነ ላለው ሰላም ምስጋና አቅርበዋል። አባገዳዎች ሃዳ ሲንቄዎችና የሀገር ሽማግሌዎች የሰላም አማራጭን ለማስፋት ያደረጉትን ጥሪ ተቀብለው ለመጡ አካላት መንግሥት ተገቢውን እገዛ ያደርጋል ብለዋል። ፅንፈኝነት ቦታ የለውም ያሉት አቶ ሽመልስ መንግሥት የጀመረውን የህግ የማስከበርና የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ስራን አጠናክሮ በማስቀጠል የሰላምና የልማት ደንቃራዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ተናግረዋል። የሰላም አማራጭ ዕድሉ አሁንም ሰፊ መሆኑን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ የሸኔ ቡድን አባላት ከጥፋት መንገድ እንዲመለሱ ዳግም ጥሪዬን አቀርባለሁ ብለዋል። የደረስንበትን ውጤት የምንለካው የህዝቡን የመልማት ፍላጎትና ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ አንፃር በሰራነው ስራ ነው ሲሉ ነው ፕሬዚዳንት ሽመልስ ከጨፌው አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት። ክልሉንም ሆነ ኢትዮጵያን ከድህነትና ኋላቀርነት፣ ከስንዴ ልመናና ተረጂነት ለማላቀቅ የተጀመሩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል። በየደረጃው ያለው አመራር አሁን በተገኙት ስኬቶች መዘናጋት ሳይሆን ለተሻለ ልማትና ዕድገት ራሳችንን ማዘጋጀት አለብን ብለዋል። አሁን በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት የተመዘገቡ ስኬቶች እያደገ ለመጣው የክልሉ ገቢ የጎላ ሚና ቢኖረውም ክልሉ ካለው የኢኮኖሚ አቅም አንፃር በበጀት ዓመቱ የሰበሰብነው ገቢ ዝቅተኛ በመሆኑ በአዲሱ በጀት ዓመት ገቢ የመሰብሰብ አቅማችንን አሟጠን በመጠቀም የተሻለ ገቢ ማስገባት ቀዳሚ ተግባራችን ነው ብለዋል። በቤተሰብ ደረጃ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ህዝቡን ያሳተፈ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን እውን በማድረግ ከድህነትና ኋላቀርነት መውጣት ይኖርብናል ሲሉም ነው የገለፁት። ''በዚህም አርሶአደሩና አርብቶ አደሩ በጥራት፣ በፍጥነትና በብዛት ማምረት አለበት'' ያሉት ፕሬዚዳንት ሽመልስ የሚመረተው ምርት ገበያ ተኮር መሆን እንዳለበትም አስገንዝበዋል። ቁጠባን የህዝቡ ባህል በማድረግና ከሚያገኘው ገቢ በመቆጠብ በስፋት ወደ ኢንቨስትመንት እንዲሻገር ማስቻል ጊዜ ሊሰጠው የሚገባ አይደለም ብለዋል። ጨፌው የ2016 ዓ.ም የስራ አፈፃፀምን እና የ2017 ዓ.ም መነሻ ዕቅድን በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።  
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ የውይይት መድረኮች የዳበረ የዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት ጥሩ መሰረት የሚያኖር ነው- የፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት
Jul 21, 2024 135
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 14/2016 (ኢዜአ)፦ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ የውይይት መድረኮች ሀገራዊ ችግሮችን በጋራ ለመፍታትና የዳበረ የዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት ጥሩ መሰረት የሚያኖር መሆኑን የፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት በወቅታዊና ዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር አድርገዋል። በመድረኩ ላይ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ደስታ ዲንቃን ጨምሮ ሌሎችም አመራሮችና የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ተገኝተዋል። የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ደስታ ዲንቃ፤ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የመነጋገር ባህልን በማጎልበት ሀገራዊ ችግሮችን በጋራ የመፍታት ልምድ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል። በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመወያየት መንግስት እያሳየ ያለውን ቁርጠኝነት አድንቀው፤ ፓርቲዎችም ለዚሁ ዝግጁ መሆን አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ የውይይት መድረኮች ሀገራዊ ችግሮችን በጋራ ለመፍታትና የዳበረ የዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት ጥሩ መሰረት የሚያኖር መሆኑንም ገልጸዋል። የዛሬው መድረክ ዓላማም በፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ የሚፈቱትን በጋራ ለመፍታት የሚያስችል ውይይት መሆኑን ጠቅሰዋል። ለህዝብና ለትውልድ ተስፋ የሚሆኑ ዓላማዎችን በመሰነቅ ኢትዮጵያን ከችግር ለማውጣት በጋራ ልንቆምና ልንሰራ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።   በብልፅግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ባሕል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ እና የጋራ ምክር ቤቱ ስራ አስፈፃሚ አባል መለስ ዓለሙ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመመካከር ሂደት አዲስ የፖለቲካ ባህል ጅማሮ መሆኑን ገልጸዋል። በመነጋገር ሀገራዊ ጥቅሞችን ማስጠበቅ፣ ችግሮችን መፍታትና መልካም ነገሮችን ማስቀጠል የሚቻል መሆኑን ተናግረዋል። ሀገር እየመራ ያለው ብልጽግና ፓርቲ የዳበረ የዴሞክራሲ ስርአት ለመገንባት በጽናትና በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።    
መከላከያ ሰራዊት ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት መስራቱን አጠናክሮ ይቀጥላል -የደቡብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ሰለሞን ኢተፋ
Jul 21, 2024 159
አዳማ፤ሀምሌ 14/2016 (ኢዜአ)፦ መከላከያ ሰራዊት በሚያከናውናቸው የሰላም ማስፈንና ሌሎች ተግባራት ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት መስራቱን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የደቡብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ሰለሞን ኢተፋ አስታወቁ። የደቡብ ዕዝ 202ተኛ ኮር የ30ኛ ነበልባል ክፍለጦር ሶስተኛ አመት ምስረታ በአል በአዋሽ ቢሾላ የስልጠና ማዕከል ዛሬ ተከብሯል። በበአሉ ላይ የደቡብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ሰለሞን ኢተፋን ጨምሮ ሌሎች የዕዙ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም አባገዳዎች፣ ሀደሲንቄዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ታድመዋል። የደቡብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ሰለሞን ኢተፋ በወቅቱ እንደተናገሩት 30ኛ ክፍለጦር በሚሰጠው ሀገራዊ ግዳጅ ጠንካራ የተልዕኮ አፈፃፀም ያለው መሆኑ የሚያኮራው ነው ። ክፍለጦሩ በአሁኑ ወቅት ከማህበረሰቡ ጋር በመተባበር የሰላም ማስከበር ተልዕኮውን እየተወጣ መሆኑን አመልክተዋል። መከላከያ ሰራዊቱ በሚያከናውናቸው የሰላም ማስፈንና ሌሎች ተግባራት ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት መስራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። በደቡብ ዕዝ የ202ተኛ ኮር ዋና አዛዥ ኮሎኔል ደጀኔ ፀጋዬ በበኩላቸው ሰራዊቱ ሰላም በማስከበር በከፈለው መስዋእትነት የልማት ስራዎች እየተሳለጡ መሆናቸውን ተናግረዋል ። ክፍለጦሩ የሀገሪቷን ዳር ድንበር በማስከበር ስመጥር መሆኑን የገለጹት ደግሞ የ30ኛ ክፍለጦር አዛዥ ሌተናል ኮሎኔል ለታ አንበሴ ናቸው። በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ሰላም በማስከበር ህዝቡ ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል። በቀጣይም መከላከያ ሰራዊቱ በሚያደርገው የሰላም የማስከበር ስራ ህዝቡ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም