ረቂቅ አዋጁ የኢትዮጵያን የግብር ስርዓት በማዘመን የገቢ አሰባሰብ አቅምን ለማሳደግ ያግዛል - ቋሚ ኮሚቴው - ኢዜአ አማርኛ
ረቂቅ አዋጁ የኢትዮጵያን የግብር ስርዓት በማዘመን የገቢ አሰባሰብ አቅምን ለማሳደግ ያግዛል - ቋሚ ኮሚቴው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 2/2017(ኢዜአ)፦ ረቂቅ አዋጁ የኢትዮጵያን የግብር ስርዓት በማዘመን የገቢ አሰባሰብ አቅምን ለማሳደግ የሚያግዝ መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ።
ቋሚ ኮሚቴው በፌዴራል የገቢ ግብር አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ላይ የአስረጂ መድረክ አካሂዷል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጄ በዚሁ ወቅት በቋሚ ኮሚቴው አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች የተሰጡት ምላሽና ማብራሪያዎች ግልፅና የተሻለ መረዳት መፍጠር መስቻሉን ተናግረዋል።
ማሻሻያው የግብር አከፋፈል ስርዓትን በማዘመን ግልፅነት በተሞላበትና ፍትሃዊነትን በሚያሰፍን መልኩ ማከናወን የሚያስችል በመሆኑ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
ማሻሻያው መንግስት ያስቀመጠውን አላማ የሚያሳካና በግብር ከፋዩ ዘንድ የተሻለ መረዳት የሚፈጥር መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በዚህም ቋሚ ኮሚቴው ለውጤታማነቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አብርሃም አለማየሁ(ዶ/ር) በበኩላቸው ረቂቅ አዋጁ በገቢ ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ዲጂታል ስርዓት ሲዘረጋ ለተገልጋዮች የበለጠ ጠቀሜታ እንዳለው አንስተው ለዚህም መሰረተ ልማት ከማሟላት አኳያ በቂ ዝግጅት ሊደረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ ማሻሻያው የታክስ ህጎች እንዲከበሩ ለማድረግና የመንግስትን ገቢ ለማሳደግ አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
የረቂቅ አዋጁ ዋነኛ አላማዎች ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ያለውን የግብር ጫና መቀነስ፣ የግብር መሰረትን ማስፋት፣ ለአነስተኛ የንግድ እንቅስቃሴዎች ቀላል የግብር አከፋፈል ስርዓት መዘርጋት ናቸው ብለዋል።
እንዲሁም ለኢንቨስትመንት የሚደረገውን ጥረት ማገዝ፣ የታክስ ማጭበርበርን መከላከልና ግልጽነት በሚጎድላቸው አንቀጾች ምክንያት የሚደርሱ ውጣ ውረዶችን ለማስቀረት እንደሆነም አክለዋል።