በህብረብሔራዊ አንድነት ላይ ያተኮረ ትርክት ግንባታ በውጤታማነት ተጠናክሮ ቀጥሏል - ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በህብረብሔራዊ አንድነት ላይ ያተኮረ ትርክት ግንባታ በውጤታማነት ተጠናክሮ ቀጥሏል - ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)

አርባምንጭ ፤ ሐምሌ 4/2017(ኢዜአ) ፡-በሀገሪቱ በህብረብሔራዊ አንድነት ላይ ያተኮረ ትርክት ግንባታ በውጤታማነት ተጠናክሮ መቀጠሉን የብልጽግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ተናገሩ ።
የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2018 ዕቅድ በአርባ ምንጭ ከተማ እየተገመገመ ነው።
የብልጽግና ፓርቲ ዓለም አቀፍና የሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው በፖለቲካውና፣ በዲፕሎማሲው ዘርፍ በዓለም አደባባይ ፈጣን ለውጥ እያስመዘገበች ትገኛለች ብለዋል።
ይህን ለማሳካትም የተረጋጋ የፖለቲካ ምህዳር በመፍጠር በህዝቦች መካከል ወንድማማችነትና እህትማማችነት እየተጠናከረ የመጣበት ዓመት ነው ሲሉም ገልጸዋል።
የሀገርን እድገት ወደ ኋላ ለመመለስ የሚጥሩ አካላት በህዝብና በመንግስት ትብብር ሴራቸው እየከሸፈ መምጣቱንም ገልጸዋል።
በህብረብሔራዊ አንድነት ላይ ያተኮረ ትርክት ግንባታ ሂደትም ውጤታማ በሆነ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ያነሱት ቢቂላ (ዶ/ር) ''እስካሁን የተመዘገበውን ስኬት ለማስቀጠል አበክረን እንሠራለን'' ብለዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ገብረመስቀል ጫላ በበኩላቸው ፓርቲው የህዝቡን ሁለንተናዊ ብልጽግና እያረጋገጠ ይገኛል ብለዋል።
የብሔር ብሔረሰቦችን መብት በማስከበር የተረጋጋች ሀገር የመገንባት ሂደቱም በተሻለ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።
በቀጣይም የተጀመሩ ልማቶችን በማስቀጠል የህዝቡን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ጠቁመዋል።
ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው መድረክ ከሁሉም ክልሎች የፓርቲው ህዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።