መንግስት በሁሉም መስክ የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ መሰረት የሚጥሉ ውጤታማ ተግባራትን አከናውኗል

ጎንደር፤ ሐምሌ 3/2017(ኢዜአ)፡- በተጠናቀቀው  የበጀት ዓመት  መንግስት በሁሉም መስክ የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ መሰረት የሚጥሉ  ውጤታማ  ተግባራት ማከናወኑ ተገለጸ። 

"ጠንካራ አደረጃጀት ለሁለንተናዊ ብልፅግና "  በሚል መሪ ሃሳብ የብልፅግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ የ2017 በጀት ዓመት ግምገማና የ2018  የእቅድ ትውውቅ መድረክ በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡


 

በግምገማ መድረኩ ላይ የብልፅግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ እንደተናገሩት፤  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በፓርቲው አመራር ሰጪነት ሀገርን ወደ ብልፅግና የሚያሻግሩና አለም ምስክርነቱን ጭምር የሰጠባቸው ትርጉም ያላቸው ውጤታማ ተግባራት ማከናወን ተችሏል፡፡

የኑሮ ውድነትን በመቀነስ የህዝቡን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የሚረዱ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብርና የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ተጠቃሽ የልማት ተግባራት መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

የከተሞችን እድገት ለማፋጠንና የሕዝቡንም የኑሮ ዘይቤ ለማዘመን እንዲቻል በመላ ሀገሪቱ እየተከናወኑ የሚገኙ  የኮሪደር ልማት ስራዎች ከተሜነትን በማላበስ አዲስ ተስፋና ብርሃን የፈነጠቁ ፋና ወጊ የልማት ተግባራት መሆናቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

የዚህ ትውልድ አኩሪ ድልና ታሪክ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብም ስኬት  የህዝባችን አይበገሬነትና የፓርቲያችን የአመራር ቁርጠኝነት የታየበት ነው ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትና በኢትዮጵያ ታሪክም ትልቅ አሻራ ያለው ነው ያሉት አቶ ፍቃዱ፤  የክልሉን ሰላም በማፅናት  ልማቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል አመራሩና ሕዝቡ ተቀናጅተው ያከናወኑዋቸው ተግባራት የሚደነቁ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ፓርቲው የሚመራው መንግስት በርካታ ውጤታማ ተግባራት ማከናወኑን ገልጸው፤ ዛሬም እንደ ትናንቱ በሕዝባችን ተሳትፎና በአመራሩ ቁርጠኛ ያልተሻገርናቸውን  በድል ለመወጣት መጪው ዓመት በትጋት ለመስራት ቃል የምንገባበት ነው ብለዋል፡፡ 

በብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ፍሰሃ ደሳለኝ በበኩላቸው፤  የአማራ ክልል ትልቅ የመልማትና የማደግ አቅም ያለው የተፈጥሮ ጸጋዎች ባለቤት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የክልሉ ሰላም በማፅናት  የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ብልፅግና ፓርቲ የጠራና ተሻጋሪ ሃሳብ ያለው በመሆኑ  ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ  እየተጋ እንደሚገኝ  ገልጸው፤  ፓርቲው ለሕዝቡ የገባውን ቃል አክብሮ ወደ ተግባር በማሸጋገር በኩል ሕዝባዊ አደራውን ይወጣል ብለዋል፡፡

ጎንደር የብልፅግና ትሩፋቶች ተቋዳሽ ከሆኑ የሀገራችን ቀደምት ከተሞች አንዱ ለመሆን በቅታለች ያሉት ደገሞ የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው ናቸው፡፡


 

በፌደራልና በክልሉ መንግስት በከተማዋ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች የቀደመ ገናና ስሟንና ታሪኳን ያደሰ ብሎም የኪነ ጥበብና የኪነ ህንጻ አሻራዋን በደማቁ ያጎሉ ተግባራት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የፓርቲው የአደረጃጀት ዘርፍ የአፈጻጸም ግምገማ መድረክ ላይ ከሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች የተውጣጡ የፓርቲው የአደረጃጃት ዘርፍ አመራሮች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ። 

አመራሮቹ በፌደራልና በክልሉ መንግስት እየተከናወኑ የሚገኙ የሌማት ትሩፋት፣  የኮሪደር ልማት፣ የአጼ ፋሲል አብያተ መንግስት እድሳትና የጥገና ስራ እንዲሁም የመገጭ የመስኖና የመጠጥ ውሃ  ግድብ ፕሮጀክቶች ትናንት ተዘዋውረው መጎብኘታቸውን በወቅቱ ተገልጿል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም