የኢትዮጵያና ዛምቢያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በተለያዩ መስኮች ተጠናክሮ ቀጥሏል - አምባሳደር ሮዝ ሳካላ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና ዛምቢያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በተለያዩ መስኮች ተጠናክሮ ቀጥሏል - አምባሳደር ሮዝ ሳካላ

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 3/2017(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ እና በዛምቢያ መካከል ያለው ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ግንኙነት በተለያዩ መስኮች ተጠናክሮ መቀጠሉን በኢትዮጵያ የዛምቢያ አምባሳደር ሮዝ ሳካላ ገለጹ።
በኢትዮጵያ የዛምቢያ አምባሳደር ሮዝ ሳካላ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያ እና ዛምቢያ ዘላቂ እና ዘርፈ-ብዙ ግንኙነት እንዳላቸው ገለጸዋል።
ይህም ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እና በተለያዩ ዘርፎችም እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
በተለይም ዛምቢያ ኤምባሲዋን በኢትዮጵያ ከከፈተችበት ጊዜ አንስቶ የሁለቱ አገሮች አጋርነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ ከመምጣቱም በላይ የተለያዩ የትብብር ስራዎችም እየተጠናከረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
እ.አ.አ በ2017 ሁለቱ ሀገራት የጋራ ኮሚሽን ማቋቋማቸውን ገልጸው፤ ይህም ተጨባጭ ጥቅሞችን ማስገኘቱን ጠቁመዋል።
ሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ አቅም እንዳላቸው ገልጸው፤ ከሁለቱም ወገኖች የተውጣጡ የንግድ ባለሙያዎችን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማሰባሰብ ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማሳደግ ጥረት መደረጉን አንስተዋል።
የጋራ ኮሚሽኑ በንግድና ኢንቨስትመንት በተለይም በግብርናና በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ያለውን ትስስር እንደሚያጠናክር ጠቁመዋል።
ዛምቢያ የአፍሪካን አንድነት ለማጎልበት እና አህጉራዊ አጀንዳዎችን ለማራመድ በተለያዩ መድረኮች በማደራጀት እና በመሳተፍ ንቁ ተሳትፎ እያደረገች መሆኑን ተናግረዋል ።
አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ ቋሚ ውክልና አለማግኘቷ ኢ-ፍትሃዊ ነው ብለዋል።
ዛምቢያ ለቀጣናው ኢኮኖሚያዊ ውህደት ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳደረገች ገልፀው፤ ፓን አፍሪካኒዝም እንደ መሰረታዊ መርህ እና ከእነዚህ ጥረቶች ጀርባ አንቀሳቃሽ ሃይል ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።
የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 ለአፍሪካ በርካታ እድሎችን የሚሰጥ ወርቃማ አጀንዳ መሆኑን ገልጸው፤ በትብብር መተግበር እንደሚገባ አሳስበዋል።