በዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ የተገኙ አበረታች ሥራዎች በቀጣይም ተጠናክረው ይቀጥላሉ - አቶ መለስ አለሙ - ኢዜአ አማርኛ
በዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ የተገኙ አበረታች ሥራዎች በቀጣይም ተጠናክረው ይቀጥላሉ - አቶ መለስ አለሙ

ሐረር፤ ሐምሌ 2/2017(ኢዜአ)፡- በዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ የተገኙ አበረታች ሥራዎች በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ በብልፅግና ፓርቲ የዋናው ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መለስ አለሙ ገለጹ።
የፓርቲው የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ የ2017 ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና የ2018 እቅድ ተግባቦት መድረክ በሐረር ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
አቶ መለስ አለሙ እና በብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ጌቱ ወዬሳን ጨምሮ የፓርቲው የወጣቶችና ሴቶች ክንፍ አመራሮችና ሌሎች የፌደራልና የክልል የብልፅግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ አመራሮች ተገኝተዋል።
በመድረኩ የተገኙት አቶ መለስ አለሙ እንዳሉት በ2017 በጀት ዓመት በሁሉም ዘርፍ አበረታች ሥራዎች ተከናውነዋል።
በበጀት ዓመቱ የተገኙትን ጥንካሬዎች በማስቀጠልና የተስተዋሉ ውስንነቶችን በማረም በ2018 በጀት ዓመት የተሻለ ስራ በማከናወን ለውጡን ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
የመሃል ዘመን ፈተናን የምንሻገርበትና አዲስ የማንሰራራት ዘመን መባቻ ላይ የምንገኝ በመሆኑ የ2018 እቅድ ከወትሮው የተለየ ያደርገዋል ነው ያሉት።
በተለይ በዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራትን በ2018 በጀት ዓመትም በላቀ ደረጃ የምንተገብርበት በመሆኑ ከወዲሁ ዝግጅት እና ልምምድ በማድረግ ወደ ባህል ማሻገር ይገባል ብለዋል።
መድረኩም አቅም የምንገነባበትና ትምህርት ወስደን ለቀጣይ በጀት ዓመት ዝግጅት የምናደርግበት ነው ሲሉም ገልጸዋል።
መድረኩ በክልሎች መዘጋጀቱ በየአካባቢው ያለውን ባህል ለመረዳት፣ ለመቀራረብና ያሉ ጸጋዎችን ለመረዳት እንዲሁም ተሞክሮ ለመቅሰም እንደሆነም ተናግረዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ጌቱ ወዬሳ በበኩላቸው በክልሉ በዴሞክራሲ ባህል ግንባታ የተከናወኑ ተግባራት የሴቶችና የወጣቶች ክንፍ እንዲጠናከር እንዲሁም ከሲቪል ማህበራት ጋር ተቀራርቦ የመስራት ተሞክሮን አስፍቷል ብለዋል።
በተለይም ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር የነበረውን የተራራቀ አመለካከት በመቅረፍ በልማትና በሰላም ሥራዎች ላይ ተቀራርቦ የመስራት ባህልን አስፍቷል ነው ያሉት።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው መድረክ የብልፅግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ የ2017 እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት እና የ2018 መነሻ እቅድ ቀርቦ ውይይት ከተካሄደ በኋላ ለቀጣይ አቅጣጫ ይቀመጣል ተብሎ ይጠበቃል።
ከመድረኩ ጎን ለጎን በሐረር ከተማ የተከናወኑ የልማት ስራዎች ጉብኝት እና የችግኝ ተከላ መርሀግብር እንደሚከናወን ተመላክቷል።