ኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስጠብቁ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ተግባራትን አከናውናለች - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስጠብቁ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ተግባራትን አከናውናለች - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው የ2017 በጀት ዓመት ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስጠብቁ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ተግባራት ማከናወኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው የበጀት ዓመቱን አበይት የዲፕሎማሲ ክንውኖች አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በበጀት ዓመቱ በሁሉም የዲፕሎማሲ መስኮች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቁና የሀገርን ገፅታ የሚያስተዋውቁ የዲፕሎሚሲ ስራዎች መከናወናቸውን አስታውቀዋል።
ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነትን በኤሌክትሪክ ኃይልና በመንገድ መሰረተ ልማት ይበልጥ የማጠናከርና በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ስኬታማ ሥራዎች መፈጸማቸውን አብራርተዋል።
በበጀት ዓመቱ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን በተመለከተም የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስረዳት መቻሉን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ ከተለያዩ ሀገራት ጋር በርካታ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ስምምነቶች መደረጋቸውንም ነው ያነሱት።
እነዚህ ስምምነቶች የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም የሚያስጠብቁና በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተሰሚነትና ተደማጭነት የሚያጎለብቱ ናቸው ብለዋል።
በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲም በተለያዩ ሀገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ጤንነታቸውና ክብራቸው ተጠብቆ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን ገልጸዋል።