ምክር ቤቱ የሕግ አወጣጥ፣ የክትትልና ቁጥጥር ስራን በጥናትና ምርምር በመደገፍ ውጤታማ ተግባር እያከናወነ ነው - አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ የሕግ አወጣጥ፣ የክትትልና ቁጥጥር ስራን በጥናትና ምርምር በመደገፍ ውጤታማ ተግባር እያከናወነ ነው - አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2017(ኢዜአ)፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ አወጣጥ፣ የክትትልና ቁጥጥር ስራን በጥናትና ምርምር በመደገፍ ለአካታች ልማት መሳካት የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።
አፈ ጉባኤው ይህን ያሉት "አካታችና ጠንካራ የፓርላማ ስርዓት ለሀገር በቀል እውቀትና ቀጣይነት ላለው ልማት" በሚል በተጀመረው አምስተኛው ዓመታዊ የፓርላማ ጥናትና ምርምር ኮንፍረንስ መክፈቻ መርሃ ግብር ላይ ነው።
አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የምርምር ባህልን ማሳደግ ቀጣይነት ላለው እድገት፣ ጠንካራ ምጣኔ ሃብትና ዘላቂ እድገትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።
በመሆኑም የምርምር ኮንፍረንሱ ምክር ቤቱ ለሚያወጣቸው ፖሊሲዎች፣ ህጎችና ለሚያደርገው የክትትልና ቁጥጥር ሥራ አስተዋጽኦው ከፍተኛ እንደሆነ አንስተዋል።
ምክር ቤቱ የሕግ አወጣጥ፣ የክትትልና ቁጥጥር፣ የሕዝብ ውክልና እና የፓርላማ ዲፕሎማሲ ሥራዎችን በጥናትና ምርምር የተደገፉ በማድረግ የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ እየሰራ ነው ብለዋል።
የህዝብ ቅሬታን ከመሰረቱ በጥናትና ምርምር በመለየት በሚወጡ ህጎችና ፖሊሲዎች በማካተት ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጣቸው እያደረገ መሆኑንም ጨምረዋል።
ምክር ቤቱ በቀጣይም ከምርምር ተቋማት ጋር ያለውን የትብብር ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
በአምስተኛው ዓመታዊ የፓርላማ ጥናትና ምርምር ኮንፍረንስ የፓርላማ ዴሞክራሲ ሥርዓት ትግበራ መሻሻል፣ የፓርላማ ተግባራትን ማጠናከር፣ የሕግ የበላይነት፣ አካታች አስተዳደርና ሀገረ መንግሥት ግንባታ ላይ ያተኮሩ 12 የተለያዩ ጥናታዊ ፅሁፎች እንደሚቀርቡ የወጣው መርሃ ግብር ያሳያል።
በኮንፍረንሱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፍተኛ አመራሮች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኃላፊዎች፣ ምሁራንና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።