በዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤታማ ስራዎች ወደ ላቀ ደረጃ የማሸጋገሩ ተግባር ይጠናከራል

 

ሐረር፤ሐምሌ 3/2017 (ኢዜአ)፡-በዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤታማ ስራዎች ወደ ላቀ ደረጃ የማሸጋገሩ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በብልፅግና ፓርቲ የዋና ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ መለስ ዓለሙ ገለጹ።

የብልፅግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ በሐረር ከተማ ለሁለት ቀናት ሲያካሂደው የቆየው የ2017 እቅድ አፈጻጸም ግምገማና የ2018 እቅድ ተግባቦት መድረክ ዛሬ ተጠናቋል።

በመድረኩ የፌደራልና የክልል የብልፅግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ አመራሮች እንዲሁም የፓርቲው የወጣቶችና ሴቶች ክንፍ ተሳትፈዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የዋና ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ መለስ ዓለሙ በወቅቱ እንደተናገሩት፥ በ2017 በጀት ዓመት የዴሞክራሲ ባህል እሴትን ለማጠናከር የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል።


 

የፖለቲካ ፓርቲዎች በትብብር ከመስራት አንጻር በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በጋራ ምክር ቤቶች በመደራጀት አብሮ የመስራት ባህል እየዳበረ መምጣቱን ጠቅሰዋል።

ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የተጀመሩ ስራዎች አዲስ ባህልና ልምድ እያመጡ ስለመሆኑም አንስተዋል።

የጋራ ስራዎቹ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸው፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ለዴሞክራሲ ባህል ግንባታ በቁርጠኝነት መስራታቸውን አጎልብተው እንዲቀጥሉም አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት በየደረጃው ያለው የመንግስት አካላትና ሲቪል ማህበረሰብ በጋራና በቅንጅት የሚሰሩበት ጅምር ሁኔታ መፈጠሩን ጠቅሰዋል።

በተለይ የወጣቶችና ሴቶች አስተዋጽኦን ለማላቅና ተሳትፏቸውን ይበልጥ ለማሳደግ ብሎም ተጠቃሚነታቸውን ለማጎልበት መድረኩ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም አንስተዋል።


 

በቀጣይም ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ በተቀመጡ አቅጣጫዎች መሰረት ትኩረት ተሰጥቶ እና ባህል አድርጎ እንደሚሰራም አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም