በብሔረሰብ አስተዳደሩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በብሔረሰብ አስተዳደሩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል

ሰቆጣ ፤ሐምሌ 3/2017(ኢዜአ)፦ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት መከናወናቸውን የብሔረሰብ አስተዳደሩ አስታወቀ።
የብሔረሰብ አስተዳደሩ የተጠናቀቀው በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸምን የሚገመግምና የቀጣይ 90 ቀናት ዕቅድ ማስተዋወቂያ መድረክ በሰቆጣ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የብሔረሰብ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሃይሉ ግርማይ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የሰላምና ፀጥታ ተግባር በመካሄዱ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል።
በልማት ሥራም ለመልካም አስተዳደር ምክንያት ሆኖ የቆየው የሰቆጣ አዳሪ ትምህርት ቤትን ጨምሮ የስርዓተ ምግብን ለማሻሻል በዓመት ከ360 ሺህ በላይ ጫጩት ማስፈልፈያ ማዕከል ግንባታ ስራን ማከናወን እንደተቻለ ገልጸዋል።
በተጨማሪም የመስኖ መሰረተ ልማትን በማስፋፋት የግብርና ምርታማነት እንዲያድግ መሰራቱን ጠቁመው፣ የመኽር እርሻ ምርታማነትን ለማሳደግም በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በፌደራል፣ በክልልና በወረዳ በጀት እየተገነቡ ያሉ መሰረተ ልማቶች በተቀመጠላቸው ጊዜ በጥራት ተገንብተው እንዲጠናቀቁ የድጋፍና ክትትሉ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
የአመራሩን የማስፈፀም አቅም ይበልጥ በማሳደግ በበጀት ዓመቱ የተገኙ ስኬቶችን በአዲሱ በጀት ዓመትም ለመድገም ከምንጊዜውም በላይ በቁርጠኝነት እንደሚሰራም አቶ ሃይሉ አስረድተዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ጭምር ያልተቋረጠ የጤና አገልግሎት መስጠት መቻሉን የተናገሩት ደግሞ የብሔረሰብ አስተዳደሩ ጤና መምሪያ ሃላፊ አቶ አሰፋ ነጋሽ ናቸው።
በበጀት ዓመቱ በስርዓተ ምግብ ማሻሻል እንዲሁም የወባ እና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን በመከላከልና በማከም በተሰራው ስራም የከፋ ችግር ሳይደርስ ማለፉንም ተናግረዋል።
የእናቶችና ህፃናት ህክምና ማዕከልን ጨምሮ 42 የጤና ፕሮጀክቶች እየተገነቡ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ አሰፋ፤ በጤና ተቋማቱ ዜጎችን የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።
የብሄረሰብ አስተዳደሩ የግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ አዲስ ወልዴ በበኩላቸው "በብሔረሰብ አስተዳደሩ በመስኖ ከለማው መሬት ከ700 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ተሰብስቧል ብለዋል። ይህም የአካባቢውን ገበያ ለማረጋጋት ማገዙን ተናግረዋል።
በበጋው ወቅት በ369 ተፋሰሶች ላይ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ መካሄዱን ጠቁመው፣ የለሙትን ተፋሰሶች በስነ እፅዋት ዘዴ ለማጠናከርም ችግኞች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
በመድረኩ ላይ የክልል፣ የብሔረሰብ አስተዳደሩና የወረዳ አመራሮች ተሳትፈዋል።