በሀገሪቱ ስኬቶችን ይበልጥ በማጎልበት የብልፅግና ጉዞውን ለማሳካት የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል - ኢዜአ አማርኛ
በሀገሪቱ ስኬቶችን ይበልጥ በማጎልበት የብልፅግና ጉዞውን ለማሳካት የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል

ሀዋሳ፤ ሐምሌ 3/2017 (ኢዜአ)፡- በሀገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች የተመዘገቡ ስኬቶችን ይበልጥ በማጎልበት የብልፅግና ጉዞውን ለማሳካት የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸው ተገለጸ።
የብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ የ2017 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም ግምገማና የ2018 እቅድ ላይ የሚመክር የጋራ መድረክ በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ሃላፊ ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) እንዳመለከቱት፤ ፓርቲው በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ባከናወናቸው ተግባራት በርካታ ድሎችና ስኬቶች ተመዝግበዋል።
ለተመዘገቡ ድሎችና ስኬቶች በአመራሩ፣ በአባላቱና ሕዝቡ ዘንድ የፓርቲውን አስተሳሰብ በማስረጽ የተከናወኑ ሥራዎች ጉልህ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሁለተኛው ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ መከናወኑንም አንስተዋል።
በዚህም ጥልቅ ውይይቶችን በማድረግ አመራሩ ፣ አባሉና ሕዝቡ ድሉን እንዲጋራና ለብልጽግና ጉዞ በጋራ እንዲሰራ የሚያደርግ አቅም መፍጠር መቻሉንም ተናግረዋል።
በፓርቲው በተቀረጹ የተለያዩ ኢንሼቲቮች የሕብረተሰቡን ህይወት የሚቀይሩ ተግባራት መከናወናቸው ጠቅሰው፤ የብልፅግና ጉዞውን ለማሳካት የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸዋል።
ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የተጀመረው ስራ ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑን የጠቀሱት ሃላፊው፤ መልካም አስተዳደር ማስፈን፣ የኑሮ ውድነትን ማርገብ፣ ስራ አጥነት መቀነስና መሰረተ ልማት ዘርፎች ላይ የተከናወኑ ሥራዎች የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያግዙ እንደሆኑም አብራርተዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብረሃም ማርሻሎ በበኩላቸው፤ ፓርቲው አዳዲስ ሃሳቦችን በማፍለቅና ወደ ተግባር በመቀየር ያከናወናቸው ተግባራት ተጨባጭ ውጤት ያመጡ ናቸው ብለዋል።
የፓርቲው እሳቤዎች፣ የተቀረጹ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በአመራሩ፣ አባሉና ሕዝቡ ዘንድ ለማስረጽ የፖለቲካና አቅም ግንባታው ዘርፍ በስልጠና የታገዘ ጉልህ ሚና እንዳበረከተም አንሰተዋል።
ባለፈው የበጀት ዓመት የተመዘገቡ ስኬቶችን በማስቀጠልና ጉድለቶችን በመለየት ለቀጣይ ጉዞ ውጤታማነት የመድረኩ ሚና ጉልህ መሆኑን ተናግረዋል።
ለሶስት ቀናት በሚቆየው መድረክ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች እየተሳተፉ ሲሆን፤ የመስክ ምልከታም እንደሚካሄድ ይጠበቃል።