ምርጫ ቦርድ በተለያዩ ጊዜያት ከተካሄዱ ምርጫዎች ተሞክሮ በመውሰድ ማሻሻያዎችን ማቅረቡ ተገቢ ነው - ቋሚ ኮሚቴው - ኢዜአ አማርኛ
ምርጫ ቦርድ በተለያዩ ጊዜያት ከተካሄዱ ምርጫዎች ተሞክሮ በመውሰድ ማሻሻያዎችን ማቅረቡ ተገቢ ነው - ቋሚ ኮሚቴው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 2/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተለያዩ ጊዜያት ከተካሄዱ ምርጫዎች ተሞክሮ በመውሰድ ክፍተቶችን መሙላት የሚያስችሉ ማሻሻያዎችን ማቅረቡ ተገቢ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።
ቋሚ ኮሚቴው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ-ምግባር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ላይ የአስረጂ መድረክ አካሂዷል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ እውነቴ አለነ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተለያዩ ወቅቶች ከተካሄዱ ምርጫዎች በመነሳትና የውጪ ተሞክሮን በመቀመር የሀገሪቱን የዲሞክራሲ ስርዓት ለማሳደግ የሚያደርገው ጥረት የሚበረታታ ነው።
ቦርዱ ረቂቅ አዋጁን ሲያዘጋጅ በኢትዮጵያ አካታች የፖለቲካ አካሄድ እንዲኖር ለማድረግ ከፍ ያሉ ስራዎች ማከናወኑን መረዳታቸውን ጠቅሰዋል።
በዋናነትም ለወጣቶች፣ ለአካል ጉዳተኞችና ሴቶች አካታች እንዲሆን የሰጠውን ትኩረት አድንቀዋል።
በኢትዮጵያ ያለው አዳጊ ዲሞክራሲ በመሆኑ ፓርቲዎች ስህተት በሚፈጥሩበት ጊዜ ማረም ተገቢ መሆኑን ጠቁመው፤ ሕግና ስርዓትን ለማስከበርም በረቂቅ አዋጁ የተካተቱት ጉዳዮች ተገቢ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የምርጫ አስፈፃሚዎች ቁጥርን አስመልክቶ እንደየስራ ጫናው ሊሆን እንደሚገባ ያመለከቱት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ከዚህ አኳያ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ተገቢ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ምርጫን በቴክኖሎጂ ለማከናወን በረቂቅ አዋጁ የተቀመጠው ተገቢና አስፈላጊ ከመሆኑ ባለፈ ጊዜውን የዋጀ ነው ብለዋል።
ከቅሬታ ሰሚ አኳያም በቀጣይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት የሚደረግበት መሆኑን ነው ሰብሳቢው ያመላከቱት።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሜላትወርቅ ሀይሉ በሰጡት ማብራሪያ፤ ረቂቅ አዋጁ በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ወቅት በአፈጻጸም ላይ የታዩ ክፍተቶችን መፍታት የሚያስችል ማሻሻያ መደረጉን ገልፀው፤ በዋናነትም የመራጭነትና የዕጩነት ምዝገባና የእድሜ ሁኔታን ያካተቱ አንቀፆች መካተታቸውን ነው የተናገሩት።
ረቂቅ አዋጁ በተሻለ መልኩ አካታች የሆነ አካሄድ እንዲከተል የተደረገ ሲሆን፤ ለሴቶችና ለአካል ጉዳተኞችም ልዩ ትኩረት መስጠቱን አስረድተዋል።