በበጀት አመቱ በከተማዋ በተከናወኑ ስኬታማ የሰላም ተግባራት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ ነበር - የከተማዋ የምክር ቤት አባላት

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2017(ኢዜአ)፦ በበጀት አመቱ በከተማዋ በተከናወኑ ስኬታማ የሰላም ተግባራት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ እንደነበር የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባላት ተናገሩ።

3ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ እና የበጀት አመቱ ማጠቃለያ ስብሰባ እየተካሄደ ነው።

በስብሰባው ከንቲባ አዳነች አቤቤ የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት እና የ2018 በጀት ዓመት ዋና ዋና አቅጣጫዎችን ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።

በዚሁ ጊዜ በ2017 በጀት ዓመት የከተማዋን ሰላም በማስጠበቅ፣ የነዋሪዎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከማሳደግ እንዲሁም አህጉራዊና ዓለም-አቀፋዊ ሁነቶችን በማስተናገድ ስኬታማ ሥራዎች መሰራታቸውን ነው ያብራሩት።

በከተማዋ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በርካታ የጸጥታና የወንጀል ድርጊቶችን በመለየትና አስቀድሞ በመከላከል ብሎም ህጋዊ እርምጃዎችን መውሰድ መቻሉን አንስተዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አባላትም የከተማዋን ሰላምና ደህንነት ከማረጋገጥ አንጻር የተከናወኑት ተግባራት ስኬታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊና የምክር ቤቱ አባል ሊዲያ ግርማ በበጀት ዓመቱ በከተማዋ ሰላም በመረጋገጡ የልማት ስራዎች ስኬታማ በሆነ መልኩ እንዲከናወኑ በትኩረት መሰራቱን ገልጸዋል።

የከተማው ነዋሪ ህብረተሰብም በወንጀል መከላከል ሂደትና ሰላም በማስጠበቅ ሂደት ላይ የነበረው ተሳትፎ በየጊዜው እየጎለበተ መምጣቱን እንዲሁ።

ሰላም ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ልማት የማይተካ ሚና አለው ያሉት ደግሞ ሌላዋ የምክር ቤት አባል ወርቅነሽ ምትኩ (ዶ/ር) ናቸው።


 

በከተማዋ ለተመዘገቡ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ለውጦች የሰላምና ጸጥታ መረጋገጥ ትልቅ ሚና መጫወቱንም ጨምረው ተናግረዋል፡፡

ሌላው የምክር ቤት አባል ኢቲሳ ደሜ(ዶ/ር) ህዝብን ያሳተፈ የሰላምና ልማት ሥራ የተሻለ ውጤት እንደሚያመጣ አዲስ አበባ ማሳያ ናት ብለዋል።


 

ከተማዋ የአህጉራዊና አለም አቀፋዊ ተቋማት መቀመጫና የአፍሪካ መዲና በመሆኗ ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ በኩል ህብረተሰቡ ቀጣይነት ያለው ድጋፉንና ተሳትፎውን ማስቀጠል እንደሚገባ በመጥቀስ።

በከተማዋ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት እንዲረጋገጡ የምክር ቤቱ አባላት ድጋፍና ክትትላቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።

የከተማዋን ሰላም በማስቀጠል ሂደትም ነዋሪው ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል የምክር ቤት አባላቱ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም