በተለያዩ ሀገራት በችግር ውስጥ የነበሩ ከ131 ሺህ በላይ ዜጎች ተመልሰዋል - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2017(ኢዜአ)፦ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በ21 ሀገራት በችግር ወስጥ የነበሩ ከ131 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ሚኒስቴሩ በተጠናቀቀው የ2017 በጀት ዓመት ዋና ዋና የዲፕሎማሲ ሥራዎችን አስመልክተው ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ ብሔራዊ ጥቅሟን ያስከበሩ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ግንኙነት በመፍጠር፣ ቀጣናዊ ትስስር እንዲሁም አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ትብብርን ማጠናከር የሚያስችሉ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎች አከናውናለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር የሚያስችሉና ቀጣናዊ ትስስርን የሚያፋጥኑ ፍሬያማ የዲፕሎማሲ ተግባራትን ማከናወኗንም አመልክተዋል።

ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያን እውነት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስረዳት ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራዎች መከናወናቸውንም አምባሳደሩ አብራርተዋል።

የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን እንዲቋቋም በማድረግ ኢትዮጵያ የፍትሃዊ ተጠቃሚነት መሻቷን በተግባር አሳይታለች ነው ያሉት።

‎ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ለማጠናከር ለ968 የተለያዩ ሀገራት ዜጎች የትምህርት እድል መስጠቷንም ቃል አቀባዩ ጨምረው ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ ‎የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም የሚያስከብሩ 11 ስምምነቶች ተፈርመው በፓርላማ መፅደቃቸውንም ነው አምባሳደር ነብያት ጌታቸው የገለጹት።

በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ስለ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውና ስለኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በቂ ግንዛቤ በመያዝ ድጋፉን እንዲያጠናክር የሚያደርጉ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።

በበጀት ዓመቱ በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በ21 ሀገራት በችግር ውስጥ የነበሩ ከ131ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መደረጉንም አስታውሰዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበጀት ዓመቱ ‎የዜጎችን ደህንነትና ክብር የማስጠበቅ ሥራን ቀዳሚ ትኩረት ሰጥቶ መስራቱን አመልክተዋል።

‎ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንሶችን የማስተናገድ አቅሟ እያደገ መምጣቱን የጠቀሱት አምባሳደሩ፣ በቅርቡም ትላልቅ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ይካሄዳሉ ብለዋል።

ከእነዚህም ውስጥ የተባበሩት መንግስታት ሁለተኛው የሥርዓተ ምግብ ጉባኤ እና ሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከተፈቀደላቸው የቪዛ ጊዜ በላይ መቆየት ከፍተኛ ተጠያቂነትን የሚያስከትል በመሆኑ ዜጎች ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባም ነው ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ያሳሰቡት።

የኢትዮጵያን ቪዛ አግኝተው የሚመጡ የሌላ ሀገር ዜጎች ከተፈቀደላቸው የቆይታ ጊዜ በላይ መቆየት በሀገሪቱ ህግ መሰረት ቅጣት የሚያሰጥ መሆኑን በመገንዘብ ጥንቃቄ እንደያደርጉም አፅንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም