የከተማው ነዋሪዎች ሰላምን ለማፅናት እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ ለኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
የከተማው ነዋሪዎች ሰላምን ለማፅናት እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ ለኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል

ደብረብርሃን ፤ ሐምሌ 3/ 2017 (ኢዜአ)፡- የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች ከጸጥታ ሃይሉ ጎን በመሰለፍ በአካባቢው ሰላምን ለማፅናት እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ ለኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር በአካባቢው ሰላምን ለማፅናት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የእውቅና እና የምስጋና መርሃ ግብር አካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት እንደገለጹት፤ የጸጥታ ሃይሉ ከሕብረተሰቡ ጋር በመተባበር ሰላም እንዲከበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
በዚህም በከተማዋ የሚካሄዱ የኢንዱስትሪ፣ የኢንቨስትመንትና የንግድ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ጠቅሰዋል።
ይህም ስራ እድል እንዲስፋፋ፣ የገቢና ሌሎች የልማት ዘርፎች ውጤታማ እንዲሆኑ ምቹ መደላድል መፍጠሩን ገልጸዋል።
በከተማዋ አሁን ላይ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እየተካሄዱ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
የልማት ሁሉ መሰረት የሆነውን ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ሁሉ ሕብረተሰቡ ከጸጥታ ሃይሉ ጎን በመሰለፍ የተለመደ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የእውቅና እና የምስጋና መርሃ ግብሩ ዓላማም የከተማው ነዋሪዎች ከጸጥታ ሃይሉ ጎን በመሰለፍ የህግ ማስከበር ስራው ይበልጥ በውጤታማነት በማስቀጠሉ ሂደት ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ለማበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።
ከህግ አስከባሪዎች መካከል ሀምሳ አለቃ ሰይፈ ደምሰው በሰጡት አስተያየት፤ ሰላምን አፅንቶ በማስቀጠል ለልማት የተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ይበልጥ ለማጠናከር ከሕብረተሰቡ ጋር ተቀናጅተወ በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
ሌላው የመርሃ ግብሩ ተሳታፊ ፈለቀ በየነ በበኩላቸው፤ የአካባቢውን ሰላም በማፅናት የልማት ስራዎቻቸው ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በቁርጠኝነት እንሰራለን ብለዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የጎዳና ላይ ትርኢቶችና ሌሎች ዝግጅቶች ተካሂደዋል።