ተቋማት በጥናት የቀረቡ የፖሊሲ ምክረ ሀሳቦችን ወደ ተግባር መቀየር ይገባቸዋል- የምክር ቤቱ አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
ተቋማት በጥናት የቀረቡ የፖሊሲ ምክረ ሀሳቦችን ወደ ተግባር መቀየር ይገባቸዋል- የምክር ቤቱ አመራሮች

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 2/2017(ኢዜአ)፦ ተቋማት በጥናት የቀረቡ የፖሊሲ ምክረ ሀሳቦችን ወደ ተግባር መቀየር እንደሚገባቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አመራሮች ገለጹ።
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አመራርና አባላት ጋር ባካሄደው የምክክር መድረክ የተለያዩ የጥናትና ምርምር ውጤቶች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች መድረኩ በፖሊሲ ዙሪያ ሰፊ ግንዛቤ የተፈጠረበት መሆኑን ገልጸዋል።
ኢንስቲትዩቱ እያከናወናቸው ባሉ ስራዎች እና በቀረቡ የምርምር ስራዎች ዙሪያ አስተያየት እና ጥያቄዎችን አንስተዋል።
የከተማ፣ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መሀመድ አብዶ የምርምር ስራዎቹ ችግር ፈቺ መሆናቸውን በማንሳት፥ ግኝቶቹን ተቋማት እንዲተገብሯቸው ምን እየተሰራ ነው ብለዋል።
የጤና፣ ማህበራዊ፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቀሰሙ ማሞ፥ ኢንስትዩቱ ትልቅ ሀገራዊ አቅም በመሆኑ ተቋማዊ ብቃትን ለማሳደግ የሰው ኃይል ግንባታ ላይ ትኩረት እንዲሰጥ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያን በፖሊሲ ጥናት ተወዳዳሪ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ የአደረጃጀት ሥራዎች ላይ ማብራሪያ የጠየቁት ደግሞ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ኢንጂነር ስለሺ ኮሬ (ዶ/ር) ናቸው።
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፍቃዱ ጸጋ የመንግሥት ተቋማት የሚሰሩ የምርምር ስራዎችን እንዲተገብሩ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አንስተዋል።
ከዚህም ባለፈ የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በሁሉም ሚኒስቴሮች የጥናትና ምርምር የሥራ ክፍሎችን ማቋቋሙን በማንሳት፥ ኢንስቲትዩቱ የጋራ ፎረም በመፍጠር የአቅም ግንባታ ድጋፍ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
በ2018 ዓ.ም የፖሊሲ ምርምር የሚመራበትን እና የምርምር የትኩረት መስኮችን ከወዲሁ በአጀንዳ በመቅረጽ ወደ ትግበራ ለመግባት ዝግጅት መደረጉንም ጠቁመዋል።
የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ በረከት ፍስሐጽዮን በበኩላቸው፥ ኢንስቲቲዩቱ ትልልቅ ተጽእኖ ፈጣሪ የምርምር ውጤቶችን እያበረከተ መሆኑን አንስተዋል።
ተቋሙ የፖሊሲ አጀንዳዎችን በመቅረጽ፣ የተፅዕኖ ግምገማ እና የአቅም ግንባታ ስራዎችን በመተግበር ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።
ተቋሙ ከተሰጠው ሀገራዊ ተልእኮ አንጻር እያከናወናቸው ያሉ ስራዎችን አጠናክሮ እንዲቀጥል ምክር ቤቱ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር መሰረት ኃይሌ በበኩላቸው፥ የኢንስቲትዩቱ የጥናት ግኝቶች ለፖሊሲዎች ዝግጅት እና ምክር ቤቱ ለሚያጸድቃቸው አዋጆች ተጨማሪ አቅም እየፈጠሩ መሆኑን ገልጸዋል።
የተጠኑ የምርምር ውጤቶች ተግባራዊ መደረጋቸውን መከታተል እና መፈተሽ እንደሚገባም አፅንኦት ሰጥተዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሜቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጆ፥ የምርምር ተቋማት የሚያወጧቸው ምክር ሀሳቦች ለተቋማት ተደራሽ እየተደረጉ መሆናቸው የሚበረታታ ነው ብለዋል።
የመንግሥት ተቋማትም በጥናት ላይ ተመስርተው የቀረቡ የፖሊሲ ምክረ ሀሳቦችን ወደ ተግባር መቀየር እንደሚገባቸው አስንገዝበዋል፡፡
ለዚህም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፖሊሲ ምርምር ኢንስቲትዩት ክትትል የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው ነው ያሉት።
በመድረኩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶን ጨምሮ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች፣ ምክትል ሰብሳቢዎች፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና ባለድርሻ አካላት ታድመዋል።