በምግብ ራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት ኮሞሮስ ከኢትዮጵያ ብዙ ልምድ መውሰድ ትችላለች-ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀስላሴ - ኢዜአ አማርኛ
በምግብ ራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት ኮሞሮስ ከኢትዮጵያ ብዙ ልምድ መውሰድ ትችላለች-ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀስላሴ

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 1/2017(ኢዜአ)፦በምግብ ራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት ኮሞሮስ ከኢትዮጵያ ብዙ ልምድ መውሰድ ትችላለች ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀስላሴ ተናገሩ።
ኮሞሮስ ባቀረበችው ግብዣ መሰረት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀስላሴ 50ኛው የኮሞሮስ የነፃነት በዓል በሞሮኒ ከተማ ሲከበር መታደማቸው የሚታወስ ነው፡፡
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀስላሴ ከኮሞሮስ ለቀረበላቸው ግብዣ ምስጋና አቅርበው፥ ኢትዮጵያ ከኮሞሮስ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የማሸጋገር ፍላጎት እንዳላት አብራርተዋል፡፡
ከ120 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ያላት ኢትዮጵያ በምግብ ምርት ራሷን ለመቻል ባደረገችው ጥረት ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቷንም አስገንዝበዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም፥ ኮሞሮስ በግብርናው ዘርፍ ከኢትዮጵያ ትልቅ ተሞክሮ ልትወስድ እንደምትችል አስረድተዋል፡፡
የኮሞሮስ ፕሬዝዳንት አዛሊ አሱማኒ በበኩላቸው፥ የፕሬዝዳንት ታዬ በዚህ በዓል ላይ መገኘት ኢትዮጵያ ለኮሞሮስ ያላትን ክብር የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ፕሬዝዳንት አዛሊ አሱማኒ፥ ከፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀስላሴ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ፍሬያማ ውይይትን ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።፡
በውይይታቸው ወቅትም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ማዕከል መሆኗንም ገልጸዋል፡፡
ፕሬዝዳንት አዛሊ ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለው ኢኮኖሚያዊ ለውጥ አፍሪካውያንን ለተሻለ እድገት የሚያነሳሳ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ለውጥ ማሳያ የሆነውን የኢትዮጵያ አየር መንገድም ኮሞሮስን ከተቀረው አፍሪካ እና አለም ጋር በማገናኘት ረገድ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
የኮሞሮስ ፕሬዝዳንት አዛሊ አሱማኒ፥ ከኢትዮጵያ ስንዴ የመግዛት ፍላጎት እንዳላትም ተናግረዋል፡፡