ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን የተመድ የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ አሰናበቱ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 2/2017(ኢዜአ)፦ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ረዳት ዋና ፀሐፊ እና በኢትዮጵያ የድርጅቱ የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ ራሚዝ አላክባሮቭን(ዶ/ር) አሰናበቱ።

ፕሬዝዳንት ታዬ በዚሁ ወቅት ዶክተር ራሚዝ አላክባሮቭ በስራ ዘመናቸው ላበረከቱት አስተዋፅኦና የተመድ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ላሳዩት ቁርጠኝነት አድናቆትና ምስጋና አቅርበዋል።

ዶክተር ራሚዝ ኢትዮጵያ እና የመንግስታቱ ድርጅት ስኬታማ ትብብር እንዲኖራቸው ማድረጋቸውን ያወሱት ፕሬዝዳንቱ፥ በቀጣይ ተልዕኳቸው ስኬታማ እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

የተመድ ረዳት ዋና ጸሐፊ እንዲሁም በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ ዶክተር ራሚዝ አላክባሮቭ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በኢትዮጵያ ትርጉም ያለው ጊዜ ማሳለፋቸውን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር፣ የከተማ እና የገጠር የኮሪደር ልማት እንዲሁም ሌሎች የለውጥ ሥራዎች አስደናቂ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ዶክተር ራሚዝ አላክባሮቭ ጨምረውም በስራ ዘመናቸው ኢትዮጵያ እና ተመድ የልማት ትብብራቸውን ማጠናከራቸውን ገልጸዋል።

ለአብነትም የዘላቂ ልማት ግቦችን ማዕከል ያደረገ የ5 ዓመታት የትብብር ማዕቀፍ መፈረሙን አውስተው፥ ኢትዮጵያ የማይበገር የምግብ ስርዓት ለመገንባት የጀመረችውን ጥረት የሚያጠናክር እንደሆነ ጠቁመዋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያና የተመድ ትብብር ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡም አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም