የምርምር ባህልን ማሳደግና ፈጠራን ማበረታታት ቀጣይነት ላለው ሀገራዊ እድገት ወሳኝ ነው-አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ - ኢዜአ አማርኛ
የምርምር ባህልን ማሳደግና ፈጠራን ማበረታታት ቀጣይነት ላለው ሀገራዊ እድገት ወሳኝ ነው-አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 3/2017(ኢዜአ)፦ የምርምር ባህልን ማሳደግና ፈጠራን ማበረታታት ቀጣይነት ላለው ሀገራዊ እድገት ወሳኝ መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።
አምስተኛው ዓመታዊ የፓርላማ ጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ "አካታችና ጠንካራ የፓርላማ ስርዓት ለሀገር በቀል እውቀትና ቀጣይነት ላለው ልማት" በሚል መሪ ሀሳብ መካሄድ ጀምሯል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት፥ በየዓመቱ የሚካሄደው የምርምር ጉባኤ ለእውቀት መፍለቅ፣ለምርምርና ጥናት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።
ጉባኤው ምክር ቤቱ ለተሻለ ህግ ማውጣት፣ ለውጤታማ ክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም ለተሳካ የፓርላማ ዲፕሎማሲ የሚያስፈልገውን መረጃና ትንተና እንዲያገኝ እድል መፍጠሩን አስታውሰዋል።
በምጣኔ ሃብት፣ፖለቲካ፣ማህበራዊና በቴክኖሎጂ ዘርፎች የሚደረጉ ጥናትና ምርምሮች ሀገራዊ አቅምን ለመገንባትና ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ወሳኝ ናቸው ብለዋል።
ምርምር ለማንኛውም አገራዊ ልማትና እድገት መሰረት በመሆኑ በተቋምና በሀገር ደረጃ የላቀ እድገት ለማስመዝገብ ለጥናትና ምርምር ትኩረት መስጠት ተገቢ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የምርምር ባህልን ማሳደግ፣ፈጠራን ማበረታታትና እውቀትን በተግባር ማዋል ቀጣይነት ላለው እድገት ወሳኝ መሆኑን በመጠቆም በተለይም ለህግ አውጪ አካል ስራዎች የምርምር ሚና የላቀ እንደሆነም ጠቁመዋል።
ምክር ቤቱ የሚወስናቸው ውሳኔዎች፣የሚያወጣቸው ህጎችና የሚያደርገው የክትትልና ቁጥጥር ስራ ጥናትና ምርምር ላይ የተመሰረቱ እንዲሆኑ ሚናውን አጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት።
እንደ አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጻ፥ የሚወጡ ህጎችን ተቀባይነት እንዲኖራቸው በጥናት ላይ የተመሰረተ የህዝብ ፍላጎት፣አስተያየትና ቅሬታን በመሰብሰብና በመተንተን በህግ አወጣጥ ሂደት ውስጥ ማካተት ያስፈልጋል።
በተመሳሳይ ምክር ቤቱ መንግስት የሚሰራቸውን ስራዎች ለመከታተል፣ የበጀት አጠቃቀም ለመቆጣጠርና የመንግስት ፖሊሲዎችን ውጤታማነትን ለመገምገም ጥልቅ ትንተና ማድረግ ተገቢ ነው ብለዋል።
ምክር ቤቱ ለምርምር ትኩረት በመስጠት፣የምርምር ጉባኤዎችን በማዘጋጀትና የፓርላማ የምርምር ትስስር በማቋቋም ከምርምር ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከሩንም ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር) በበኩላችው፥ የቴክኖሎጂ ዕድገትን ተከትሎ የተፈጠረው የድህረ እውነት ዓለም አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ እንደሚገኝ አንስተዋል።
ይህን ለመቀልበስ በጥናት ምርምር ላይ የተመሰረተ ሥራ እና ጠንካራ ፓርላማ መገንባት እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።
በምርምር ጉባኤው ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡት በጅማ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ ተመራማሪ እውነቱ ሃይሉ (ዶ/ር)፥ ኢትዮጵያ ለዘመናት ፀንታ የቆየችው በራሷ ዕውቀትና እውነት ውስጥ በመኖሯ ነው ብለዋል።
ምክር ቤቱ በሚያወጣቸው የህግ ማዕቀፎች ውስጥ ሀገር በቀል እውቀቶችን ማካተት አለበት ያሉት ተመራማሪው፥ የሀገር በቀል እወቀቶችን ፋይዳ ማስገንዘብም እንደሚገባ አስረድተዋል።
በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የህዝብ አስተዳደርና ኢኮኖሚ መምህርና ተመራማሪ ዳንኤል በየራ በበኩላቸው፥ ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አካታችነት አንጻር የተገኙ ውጤቶችና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ጥናታዊ ፅሁፍ አቅርበዋል።
ከግሉ ዘርፍ፣ ከትምህርት፣ ከመሰረተ ልማት፣ ከጤና አካታችነት አንጻር ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቅሰው፥ ምክር ቤቱ ለላቀ ስኬት የክትትልና ቁጥጥር ስራውን ማጠናከር እንዳለበት ጠቁመዋል።
በአምስተኛው ዓመታዊ የፓርላማ ጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ የፓርላማ ዴሞክራሲ ሥርዓት ትግበራ መሻሻል፣የፓርላማ ተግባራትን ማጠናከር፣ የሕግ የበላይት፣አካታች አስተዳደርና ሀገረ መንግሥት ግንባታ ላይ ያተኮሩ 12 የተለያዩ ጥናታዊ ፅሁፎች በምሁራን እንደሚቀርቡ የወጣው መርሃ ግብር ያሳያል።