በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርኃ ግብር አስደማሚ ለውጥ የታየበት ነው - ተመድ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርኃ ግብር አስደማሚ ለውጥ የታየበት ነው - ተመድ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 2/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለው በአለም ትልቁ የሆነው የአረንጓዴ ዐሻራ መርኃ ግብር አስደማሚ ለውጥ የታየበት ነው ሲሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ረዳት ዋና ጸሀፊ እንዲሁም በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ ራሚዝ አላካባሮቭ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀስላሴ የስራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን የተመድ ረዳት ዋና ጸሀፊ እንዲሁም በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ ራሚዝ አላካባሮቭ(ዶ/ር)ን አሰናብተዋል፡፡
በዚህ ወቅት ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀስላሴ በተመድ ረዳት ዋና ጸሀፊው የስራ ዘመን ኢትዮጵያ ከመንግስታቱ ድርጅት ጋር ስኬታማ የሚባል ትብብር እንደነበራት ገልጸዋል፡፡
በውይይታቸውም በኢትዮጵያ እና በተመድ መካከል የቆየው መልካም ትብብር ተጠናክሮ በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ መምከራቸው ተመላክቷል፡፡
የተመድ ረዳት ዋና ጸሀፊ እንዲሁም በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ ራሚዝ አላካባሮቭ(ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ባለፉት 2 ዓመታት በኢትዮጵያ አስደናቂ ለውጦችን ተመልክቻለሁ ብለዋል።
በኢትዮጵያ ትርጉም ያለው ጊዜ ማሳለፋቸውን ጠቁመው በተለይ በኢትዮጵያ በከተማ እና በገጠር እየተከናወነ ባለው ሰፊ የለውጥ ስራ መደነቃቸውን ተናግረዋል፡፡
በከተሞች የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት አማካኝነት አዲስ አበባ እና ሌሎች የክልል ከተሞች እየተቀየሩ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ሌላው አስደማሚ ለውጥ ደግሞ በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለው በአለም ትልቁ የሆነው የአረንጓዴ ዐሻራ መርኃ ግብር መሆኑን አንስተዋል፡፡
በቢሊዮን የሚቆጠር ችግኝ የሚተክል ሀገር አላየሁም ያሉት ምክትል ዋና ጸሀፊው ኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው የልማት ግብን በማሳካት ረገድ ረጅም ርቀት ተጉዛለች ብለዋል።
ዶክተር ራሚዝ አላካባሮቭ ጨምረውም በቀጣይም በኢትዮጵያ እና በተመድ መካከል ትብብሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
ከሳምንታት በፊት የተፈረመው የስድስት ቢሊዮን ዶላር የትብብር ስምምነት በቀጣይ አምስት አመታት የኢትዮጵያን ትላልቅ የልማት ዕቅዶች በመደገፍ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወትም ገልጸዋል፡፡