አካባቢ ጥበቃ
የአዲስ አበባን የደን ሽፋን 30 በመቶ ለማድረስ በሚደረገው ጥረት የሕዝቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ 
Jul 22, 2024 173
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 15/2016 (ኢዜአ)፦የአዲስ አበባን የደን ሽፋን 30 በመቶ ለማድረስ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሕዝቡ ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ። የአዲስ አበባ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ እንዲሁም ተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች በለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር አካሂደዋል። የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባና የኢንዲስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፤ በመዲናዋ በዘንድሮው ዓመት 20 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ርብርብ እየተደረገ ነው።   በመርኃ ግብሩ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርሰውን አሉታዊ ተፅኖን ለመከላከል የሚያስችሉ ለደን፣ ለከተማ ውበትና ለምግብነት የሚውሉ ችግኞች በስፋት እየተተከሉ መሆኑን ተናግረዋል። በመዲናዋ ባለፉውት ዓመት የተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ 86 በመቶው ማፅደቅ መቻሉን ተናግረዋል። የአዲስ አበባን የደን ሽፋን ከነበረበት 15 ነጥብ 8 በመቶ ወደ 30 በመቶ ለማሳደግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል የመዲናዋ ነዋሪዎች ለዚህ ስኬት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል። በመርኃ ግብሩ ከተሳተፉ ሠራተኞች መካከል፤ በርኼ ገ/መድንና ባንች ፀኃይ በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የተቀመጠው ግብ እንዲሳካ በተከታታይ አሻራቸውን በማኖር የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል። ችግኞችን ከመትከል ባለፈ የተተከሉ ችግኞች ለፍሬ እንዲበቁ እያደረጉት ያለውን እንክብካቤ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል። በአገር አቀፍ ደረጃ የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር "የምትተክል አገር የሚያፀና ትውልድ "በሚል መሪ ኃሳብ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቀዶ እየተሰራ ይገኛል።      
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የብዝኃ ህይወት መመናመንን በማስቀረት የስርዓተ ምህዳር ሚዛንን እያስጠበቀ ነው - የኢትዮጵያ ብዝኃ ህይወት ኢንስቲትዩት
Jul 22, 2024 94
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 15/2016(ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የብዝኃ ህይወት መመናመንን በማስቀረት ዘላቂ የስርዓተ ምህዳር ሚዛንን እያስጠበቀ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ብዝኃ ህይወት ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡ ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ ስፋቷ 60 በመቶ በደን ኃብት የተሸፈነ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል። ይህ የደን ሽፋን በጊዜ ሂደት ወደ 40 በመቶ ከመቀነሱ ባለፈ በተደጋጋሚ የሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ክስተቶች ምክንያት ወደ 3 በመቶ መውረዱ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። በዚህም የሀገር በቀል ዕጽዋትንና እንስሳትን ጨምሮ የብዝኃ ህይወት ሀብት መመናመንን ያስከተለ ሲሆን የስርዓተ ምህዳር መዛባትንም ፈጥሮ ቆይቷል። የዓለም ፈተና የሆነው የአየር ንብረት ለውጥ ችግሩን አባብሶት የቆየ ሲሆን፥ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ውጥን በ2011 ዓ.ም የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ቁልፍ መፍትሔ ሆኖ መጥቷል። ባለፉት አምስት ተከታታይ ዓመታት ህዝብን በማስተባበር ከ32 ቢሊዮን በላይ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፥ ሀገር በቀል ዕጽዋትም ይገኙበታል። በዚህም የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ማደጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ባስጀመሩበት ወቅት ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ብዝኃ ህይወት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፈለቀ ወልደየስ(ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የብዝኃ ህይወት መመናመንን እያስቀረ ነው።   መርሐ ግብሩ በኢትዮጵያ በመጥፋት ላይ ለነበሩ ሀገር በቀል ዕጽዋት ትኩረት መስጠቱን ጠቅሰው፥ በዚህም በየዓመቱ በርካታ ችግኞች መተከላቸውን ነው ያብራሩት። የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለብዝኃ ህይወት ጥበቃ ትልቅ እድል መሆኑን የገለጹት ፈለቀ(ዶ/ር)፤ ኢንስቲትዩቱም እየተመናመኑ ያሉ ዕጽዋትን ጠብቆ ለማቆየትና ለማባዛት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ሀገር በቀል ዕጽዋትን መትከል የአካባቢ ስርዓተ ምህዳርን ሚዛን በዘላቂነት ከማስጠበቅ ባለፈ በመጥፋት ላይ ያሉ ዕጽዋቶች እንዲያገግሙ ሰፊ እገዛን እንደሚያደርግ አስረድተዋል። ኢንስቲትዩቱ "የምትተክል ሀገር የሚያጸና ትውልድ" በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ በሚገኘው የዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ እንደ ኮሶ፣ ብርብራ፣ የሀበሻ ጽድ፣ ቀርከሃና ሌሎች 4 ሚሊዮን የሚጠጉ ሀገር በቀል ችግኞች ማዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ እነዚህ ችግኞች በኢንስቲትዩቱ ስር ባሉ ዘጠኝ ማዕከላትና ለሌሎች ተቋማት ተደራሽ መደረጋቸውን አመላክተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሰኔ 22 ቀን 2016 ዓ.ም በደቡብ ወሎ ዞን ሐይቅ ከተማ ባስጀመሩት የዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ7 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ለመትከል ታቅዷል።
የመዲናዋን ወጣቶች በማሳተፍ በርካታ የበጎ ፍቃድ ተግባራትን እያከናወንን ነው
Jul 21, 2024 218
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 14/2016(ኢዜአ)፦ የመዲናዋን ወጣቶችና የስፖርት ቤተሰብ በማሳተፍ በርካታ የበጎ ፍቃድ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ገለጸ። የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ "የምትተክል ሀገር ፤ የሚያፀና ትውልድ "በሚል መሪ ቃል የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በእንጦጦ ፓርክ አከናውኗል ። በመርሃ ግብሩ የተገኙት የቢሮው ሃላፊ አቶ በላይ ደጀን ቢሮው የመዲናዋን ወጣቶችና የስፖርት ቤተሰቦች በማሳተፍ በርካታ የበጎ ፍቃድ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡ በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በከተማ አስተዳደሩ 17 ሚሊየን ችግኞች እንደሚተከሉ አንስተዋል ፡፡ ከዚህ ውስጥ 30 ሺህ ችግኞች በወጣቶችና ስፖርት ቢሮ እንዲተከሉ በከተማ አስተዳደሩ መሰጠቱን ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም በዛሬ ዕለት በከተማው ከሚገኙ 11 ክፍለ ከተሞች የተወጣጡ ወጣቶች ፣ የስፖርት ቤተሰቦች፣ አንጋፋና ታዋቂ አትሌቶች፣ የስፖርት ክለብ ደጋፊዎች እና በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች በእንጦጦ ፓርክ በመገኘት 20 ሺህ ችግኝ መትከላቸውን አስታውቀዋል ፡፡   በዘንድሮ ዓመት እንደ ሀገር በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የተያዘው ውጥን ግቡን እንዲመታ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አሳስበዋል ፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ እግር ኳስ ቡድን ደጋፊዎች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አንዷለም ጌታቸዉ ውብና ጽዱ ኢትዮጵያን ለመፍጠር በተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ተሳታፊ በመሆኑ መደሰቱን ተናግረዋል ፡፡ ጽዱ አካባቢን መፍጠርና ንጹህ አየር ማግኘት ለቀጣይ ትውልድም የሚጠቅም በመሆኑ የተጀመረው የችግኝ ተከላ ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል ብለዋል ፡፡ ወጣት አቶ አብዱ ለጃ በበኩሉ ችግኝ መትከል ለሀገር ጠቃሚ መሆኑን በመገንዘብ በየዓመቱ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ ተሳታፊ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡ ችግኝ ከመትከል ባለፈ የሚተከሉ ችግኞችን የመንከባከብ ልምድ እንዳለው በመግለጽ ሁሉም ችግኝ ከመትከል ባለፈ መንከባከብን ልማድ ማድረግ አለበት ብሏል ፡፡ በዘንድሮ የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ 2 ሚሊየን በላይ ወጣቶች እና ስፖርት ቤተሰቦች በ14 የበጎ ፍቃድ ተግባራት ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኙ አክለዋል ፡፡      
ተፈጥሮን ተንከባክቦ የማቆየት ሀላፊነት የሁላችንም ከመሆኑም ባሻገር የአየር ንብረት ለውጥ ያመጣውን ችግር ለማስተካከል ብቸኛው አማራጭ ነው
Jul 20, 2024 239
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 13/2016 (ኢዜአ)፦ ተፈጥሮን ተንከባክቦ የማቆየት ሀላፊነት የሁላችንም ከመሆኑም ባሻገር የአየር ንብረት ለውጥ ያመጣውን ችግር ለማስተካከል ብቸኛው አማራጭ ነው ሲሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ተናገሩ። "የምትተክል ሀገር የሚያፀና ትውልድ" በሚል መሪ ሀሳብ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በተገኙበት የ2016 ዓ.ም የክረምት የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በድሬዳዋ ተካሂዷል። መርሃ ግብሩ በድሬዳዋ አስተዳደር ቢዮአዋሌ ክላስተር አዳዳ ገጠር ቀበሌ ተከናውኗል።   አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር ለቀጣዩ ትውልድ ተፈጥሮን ተንከባክበን የማቆየት ሃላፊነት የሁላችንም ከመሆኑም ባሻገር የአየር ንብረት ለውጥ ያመጣውን ችግር ለማስተካከል ብቸኛው አማራጭ ነው ብለዋል። ዘንድሮ በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞችን በመትከልና የደን ሽፋንን በማሳደግ የተጎዱ መሬቶችን ለመጠገን መረባረብ እንደሚገባ ገልፀዋል። በመሬት መሸርሸር ምክንያት ምርታማነት በመቀነሱ የአርሶ እና አርብቶ አደሩን የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ በምግብ ሰብል ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ፈታኝ አድርጎት እንደቆየ መጠቆማቸውን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል  የክረምት የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ዕቅድን ለማሳካት ርብርብ እየተደረገ ነው - ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን 
Jul 20, 2024 176
አሶሳ ፤ ሐምሌ 13 ቀን 2016(ኢዜአ)፡- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የክረምት የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ዕቅድን ለማሳካት የተቀናጀ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን አስታወቁ። የክልሉ ከፍተኛ አመራር አባላት በአሶሳ ዞን ኡራ ወረዳ የማንጎ ክላስተር ችግኝ ተከላ ዛሬ አካሂደዋል። ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን በዚህ ወቅት፤ በክልሉ ሰኔ 23ቀን 2016 ዓ.ም የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ በተከላ እና በእንክብካቤ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቀዋል። በክረምቱ የታቀደውን ለማሳካት የአመራር አባላት ህብረተሰቡን በማስተባበር ጠንካራ ርብርብ እያደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰው በቅርቡ በአንድ ጀምበር ብዛት ያለው ችግኝ ለመትከል የጉድጓድ ቁፋሮ ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑንም ገልጸዋል።   ህብረተሰቡ መረሃ ግብሩ በይፋ ከተጀመረ አንስቶ በተፈጥሮ ሃብት ክብካቤ እና ጥበቃ የሚያደርገውን ጥረት እንዲያጠናክር አቶ አሻድሊ መልዕክት አስተላልፈዋል። የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ባበክር ሀሊፋ፤ የተተከሉ ችግኞች በአግባቡ እንክብካቤ እንዲደረግላቸው ዘላቂ ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ በቅርቡ ወደ ትግበራ እንደሚገባ አስታውቀዋል። የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ወይዘር ሀጂራ ኢብራሂም በበኩላቸው፤ የክልሉ ሴቶች አደረጃጀቶችን በመጠቀም የተቀናጀ ተከላና እንክብካቤ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል። በችግኝ ተከላው መረሃ ግብር ላይ የክልል፣ የዞንና የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራር አባላት ተሳትፈዋል።  
ጫካ ፕሮጀክት አዲስ አበባን ማራኪ ገጽታ የሚያላብስና ኢትዮጵያን በበጎ መልኩ የሚያስተዋውቅ ነው - ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን 
Jul 20, 2024 202
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 13/2016(ኢዜአ)፦ጫካ ፕሮጀክት አዲስ አበባን ማራኪ ገጽታ የሚያላብስና ኢትዮጵያን በበጎ መልኩ የሚያስተዋውቅ ነው ሲሉ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ተናገሩ። ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች በጫካ ፕሮጀክት አረንጓዴ አሻራቸውን ያሳረፉ ሲሆን፤ በፕሮጀክቱ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችንም ጎብኝተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ታህሳስ 13 ቀን 2016 ዓ.ም በውጭ ሀገራት የተወለዱ ሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው እንዲመጡ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል። ይህንን ተከትሎም ከዚህ ቀደም በሁለት ዙር የሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገር ቤት መጥተው በተለያዩ ተግባራት ተሳትፈዋል። አሁን ደግሞ በሶስተኛ ዙር በርካታ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው የመጡ ሲሆን፤ በዛሬው እለትም የሁለተኛ ትውልድ ታዳጊዎች የጫካ ፕሮጀክትን ጎብኝተዋል። በጉብኝቱ ከተሳተፉት መካከል ከአሜሪካ የመጣው ታዳጊ ኢዮሲያስ ዓለማየሁ፤ ፕሮጀክቱ እጅግ ውብና የሚያስደስት መሆኑን ተናግሯል። በፕሮጀክቱ እየተከናወኑ ያሉ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ለአዲስ አበባ ከተማ የተለየ ውብትና ድምቀት እንደሚሆኑም ነው የጠቆመው። የሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን አባላትም ወደ ሀገራቸው መጥተው ፕሮጀክቱን መጎብኝት እንዳለባቸውም ገልጿል። ሌላኛዋ ከአሜሪካ የመጣችው ታዳጊ ኣመኒ አሊ፤ ፕሮጀክቱ እጅግ ውብ መሆኑን ገልጻ፤ ይህም ሰዎች ከተለያዩ አገራት ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ እድል የሚፈጥር ነው ብላለች። የፕሮጀክቱ ተፈጥሯዊ ገጽታ የተለየ የደስታ ስሜት እንደሚፈጥርም ነው የተናገረችው። ከጀርመን የመጣችው ታደጊ ኩሽማ አሊ መሀመድ፤ በኢትዮጵያ ቆይታዋ ብዝሃ ባህሎችና ማንነቶች መኖራቸውን እንደተገነዘበች ጥቅሳ፤ ይህም እጅግ ደስ እንዳሰኛት ተናግራለች። በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም ለአካባቢ መጠበቅ ተግባራዊ ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን ተናግራለች። ጫካ ፕሮጀክት እጅግ ማራኪ ገጽታ እንዳለው ጠቅሳ፤ ፕሮጀክቱ ለአዲስ አበባ አዲስ ገጽታ የሚሰጥና ነዋሪዎችም መዲናዋን በተለየ አቅጣጫ እንዲመለከቱ የሚያደርግ ነው ብላለች። ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ጫካ ፕሮጀክትን በመጎብኘት የኢትዮጵያን ማራኪ ገጽታ እንዲገነዘቡ ጥሪ ያቀረበው ደግሞ ከአሜሪካ የመጣው ታዳጊ ናትናኤል ሃብታሙ ነው።    
በጫካ ፕሮጀክት አረንጓዴ አሻራችንን በማሳረፋችን ልዩ  የደስታ ስሜት ፈጥሮብናል - ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን
Jul 20, 2024 118
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 13/2016(ኢዜአ)፦ በጫካ ፕሮጀክት አረንጓዴ አሻራችንን በማሳረፋችን ልዩ የደስታ ስሜት ፈጥሮብናል ሲሉ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ተናገሩ። ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች በጫካ ፕሮጀክት አረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል።   ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ታህሳስ 13 ቀን 2016 ዓ.ም በውጭ ሀገራት የተወለዱ ሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው እንዲመጡ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል። ይህንን ተከትሎም ከዚህ ቀደም በሁለት ዙር የሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገር ቤት መጥተው በተለያዩ ተግባራት የተሳተፉ ሲሆን፤ አሁን ደግሞ በሦስተኛ ዙር የመጡ የሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ታዳጊዎች አረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል። በመርሃ ግብሩ ከተሳተፉት መካከል ከደቡብ አፍሪካ የመጣችው ታዳጊ ዘፍጥረት እሱእንዳለ፤ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት አረንጓዴ አሻራዋን በማሳረፏ እጅግ መደሰቷን ተናግራለች። ሁሉም ትውልደ ኢትዮጵያዊ ወደ ሀገሩ በመምጣት ባህሉንና ማንነቱን ማወቅ እንዳለበትም ነው የተናገረችው።   ከካናዳ የመጣው ታዳጊ ኢዩኤል ያሬድ በበኩሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን የተለየ ጥሪ በማቅረባቸው አመስግኗል። በቆይታውም እጅግ ያማረ ጊዜ እያሳለፈ መሆኑን ነው የተናገረው። ከአሜሪካ የመጣችው ታዳጊ ክብር ሚካኤል፤ ከሚያስደስታት ተግባራት መካከል አንደኛው ዛፍ መትከል መሆኑን ገልጻ፤ ከዚህ አኳያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር መሳተፏ ልዩ ስሜት እንደፈጠረባት ተናግራለች።   ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው በመምጣት አረንጓዴ አሻራቸውን እንዲያሳርፉም ጥሪ አቅርባለች። ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ የመጀመሪያው መሆኑን የተናገረው ታዳጊ ቅዱስ ያሬድ፤ ቆይታው አስደሳች መሆኑን ነው የገለጸው።    
በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የምናደርገው ተሳትፎ ተጠናክሮ ይቀጥላል - የኃይማኖት አባቶች
Jul 20, 2024 100
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 13/2016(ኢዜአ)፦ በአረንጓዴ አሻራ ልማት መስኩ የተያዙ ሀገራዊ ግቦች እንዲሳኩ የኃይማኖት አባቶች በመርኃ ግብሩ የሚያደርጉትን ተሳትፎ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለጹ። የአዲስ አበባ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የ2016 ዓ.ም አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርኃ ግብርን ዛሬ ጀምሯል።   ጉባኤው ከተለያዩ የኃይማኖት ተቋማት የተውጣጡ የእምነት አባቶችን ያሳተፈ የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር አካሂዷል።   በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ተወካይ መላከ ጸሀይ ቆሞስ አባ ወልደ ገብርኤል እንደተናገሩት፤ የኃይማኖት አባቶች ከጸሎትና ምዕመናን በሥነ-ምግባር ከመግራት ጎን ለጎን አረንጓዴ አሻራና መሰል የልማት ሥራዎች ላይ መሳተፍ አለባቸው። በዚህም ለምዕመኑ አርአያ መሆን አለብን ያሉት አባ ወልደ ገብርኤል በአንድነት ለበጎ ዓላማ መሰለፍ አለብን ብለዋል። ዛሬ ከሁሉም ቤተ-እምነቶች ጋር በጋራ ችግኝ ተክለናል፤ አረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥል ሁላችንም የድርሻችንን ሚና መወጣት አለብን ሲሉም ተናግረዋል። የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሸህ ፈትሁዲን ሀጂ ዘይኑ በበኩላቸው አረንጓዴ አሻራና የኮሪደር ልማቱን ጨምሮ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ ድጋፍ ሊቸራቸው ይገባል ብለዋል።   ልማቱ ቀጣዩን ትውልድ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን በመገንዘብ ከኛ የሚጠበቀውን ማድረግ ከመንግሥት ጋር ተቀራርቦ መሥራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት። የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ተወካይ አባ ጴጥሮስ በርጋ በበኩላቸው አረንጓዴ አሻራ ባህል ሆኖ ቀጣይነት ባለው መልኩ ሊከናወን ይገባል ብለዋል። ለዚህ ደግሞ እኛ የኃይማኖት አባቶች ትውልዱን ማስገንዘብና ማስተማር ይገባናል ነው ያሉት። ችግኝ መትከል አንድ እርምጃ ቢሆንም መንከባከብና ለውጤት እንዲበቃ ማድረግ ደግሞ ሌላው ትኩረት የሚፈልግ ጉዳይ ነው ሲሉም ተናግረዋል።   የአዲስ አበባ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሃፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ እንዳሉት፤ ጉባኤው በአረንጓዴ አሻራ ላይ የቀረበውን ሀገራዊ ጥሪ ተቀብሎ ችግኝ በመትከል የሚጠበቅበትን ድርሻ እየተወጣ ነው። ለአብነትም ባለፉት ዓመታት ከ3 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ጉባኤው መትከሉን አስታውሰው በ2016 ዓ.ም ክረምት ወራትም ይህንን ተሳትፎ ለማጠናከር ይሰራል ነው ያሉት። በአዲስ አበባ ደረጃም የአረንጓዴ ሽፋንን ከፍ ለማድረግ በሚደረገው ርብርብ ጉባኤው የበኩሉን አሻራ ለማሳረፍ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል። የኃይማኖት ተቋማት በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ያላቸውን ሚና እንዲያጠናክሩም ነው የጉባኤው ዋና ጸሃፊ ጥሪ ያቀረቡት። በአረንጓዴ አራሻ ልማት ዘርፍ የሚያዙ እቅዶች ግባቸውን እንዲመቱ የሁላችንም አስተዋጽኦ ሊታከልበት ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
በኦሮሚያ ክልል የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ ለዘርፈ ብዙ አገልግሎት እንዲበቁ ማድረግ አለብን- ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱራህማን
Jul 20, 2024 105
አዳማ፤ ሐምሌ 13/2016(ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ ለዘርፈ ብዙ አገልግሎት እንዲበቁ ማድረግ ይጠበቅብናል ሲሉ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱራህማን ተናገሩ። የጨፌ ኦሮሚያ ዋና አፈጉባኤ፣ የጨፌው አባላትና ሌሎች የክልሉ መንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት በአዳማ ከተማ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል። ዋና አፈ ጉባኤዋ በዚሁ ወቅት እንዳመለከቱት፤ በክልሉ ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን በመንከባከብ ለውጤት ማብቃት ይገባል።   የአየር ንብረት ለውጥ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ላይ የሚያሳድረውን ጫና መቀነስ የሚቻለው በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ በስፋት መስራት ሲቻል መሆኑንም አንስተዋል። የጨፈው አባላት በየወረዳቸውና ከተሞቻቸው ሲመለሱ ለምግብና ለደን ልማት የሚውሉ ችግኞችን በመትከልና ለውጤት በማብቃት የድርሻውን መወጣት አለባቸው ብለዋል። በተለይ የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እንዲሳካ የጨፌ አባላት ህዝቡን በመቀስቀስና በንቃት በማሳተፍ የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን የጨፌው አባላት የወከላቸውን ህዝብ ጭምር በማነሳሳት የተተከሉ ችግኞችን እንዲንከባከቡ ዋና አፈ ጉባዔዋ አስገንዝበዋል።   የአዳማ ከተማ ከንቲባና የጨፌው አባል አቶ ሃይሉ ጀልዴ በበኩላቸው፤ አስተዳድሩ የጨፌው አባላት በየዓመቱ አረንጓዴ አሻራ የሚያኖሩበት ቦታ ማስረከቡን ገልጸዋል። በዚህም ካለፈው ዓመት ጀምሮ የተለያዩ አገልግሎቶች የሚሰጡ ችግኞችን እየተከሉ መሆኑን ጠቅሰው፣ ዘንድሮም የፍራፍሬ ችግኞች መተከላቸውን ተናግረዋል። ከተተከሉት ችግኞች መካከል ዘይቱን፣ አቮካዶ፣ ብርቱካን፣ ሙዝ፣ ማንጎና ፓፓያ ይገኙበታል ብለዋል። በከተማዋ ባለፉት ዓመታት የተተከሉ ችግኞች ከኮረብታማ ተራራዎች በክረምቱ የሚወርደውን ጎርፍ ከማስቀረት ባለፈ፤ የአካባቢው ሰነ-ምህዳር በመጠበቅ የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ከንቲባው ገልጸዋል። ዘንድሮም ለምግብ፣ ለደንና ለውበት አገልግሎት የሚውሉ ችግኞችን የጨፌው አባላትን ጨምሮ የፌዴራልና የክልሉ ተቋማት፣ በከተማዋ ያሉ የተለያዩ ድርጅቶችና ተቋማት እንዲሁም ህብረተሰቡ በስፋት እየተከሉ ናቸው ብለዋል። በምስራቅ ወለጋ ዞን ዲጋ ወረዳን የወከሉ የጨፌው አባል አቶ አሰፋ ዋቅጅራ፤ በአካባቢያቸው የተከሏቸው ችግኞች አድገው የተራቆተ መሬት በደን እንዲሸፈንና የተፈጥሮ ሚዛን እንዲጠበቅ አስችለዋል ነው ያሉት። በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ በወረዳው የችግኝ ተከላ ስራ መጀመሩንና የወረዳው ህዝብ በመርሃ ግብሩ በስፋት እንዲሳተፍ የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር እንደ አገር ከተረጂነት ለመላቀቅ ለተጀመረው ጉዞ ሁነኛ መንገድ ነው
Jul 19, 2024 267
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 12/2016 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር እንደ አገር ከተረጂነት ለመላቀቅ ለተጀመረው ጉዞ ሁነኛ መንገድ ነው ሲሉ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ(ዶ/ር) ተናገሩ። የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አጋዥ የሆኑ ፍራፍሬ ምርቶችን በክላስተር ማምረት ላይም ኢኒስቲትዩቱ እየሰራ መሆኑም ተገልጿል። የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢኒስቲትዩት አመራርና ሰራተኞች በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን አድአ ወረዳ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አካሂደዋል። አመራርና ሰራተኞቹ የአድአ ወረዳ የጎዲኖ ጂቱ የተቀናጀ የግብርና ማዕከል የሥራ እንቅስቃሴንም ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። የኢኒስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የአረንጓዴ አሻራ የልማት ሥራዎች እንደ አገር በሂደት ከተረጂነት ለመላቀቅ ሁነኛ መንገድ ናቸው።   አረንጓዴ ልማቱ ድርቅን ለመከላከል ከማገዙም በላይ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል። ኢኒስቲትዩቱም ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ሚና ያላቸው የፍራፍሬ ምርቶችን በክላስተር የማምረት ሥራዎች ላይ ትኩረት ማድረጉን አመልክተው ። ከዚህ ውስጥም የአቮካዶ፣ሙዝና ማንጎን ጨምሮ ለምግብነት የሚውሉ ምርቶችን በማምረትና ለአምራቾች የቴክኒክ ድጋፍ መስጠት ላይም በሰፊው እየሰራ ነው ብለዋል። በዛሬው ዕለትም በአድአ ወረዳ የአቮካዶ ችግኞችን መትከላቸውን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ በክረምት ወራት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ተመሳሳይ ችግኝ ለመትከል እቅድ መያዙንም ጠቁመዋል። የኦሮሚያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢኒስቲትዩት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ደሳለኝ ዱጉማ በበኩላቸው፤ አርሶ አደሩ የአገሪቷን የውጭ ምንዛሬ ገቢ የሚያሳድጉ የፍራፍሬ ምርቶችን እንዲያመርቱ ድጋፍ እየተደረገ ነው።   በዚህም ሰፋፊ መሬቶች በፍራፍሬ ምርቶች በክላስተር እየለማ መሆኑን ጠቁመው በምስራቅ ሸዋ ዞንም በዚሁ መልኩ ተመርቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ለውጭ ገበያ የቀረበው አቮካዶ ምርት ተጠቃሽ ነው ብለዋል። በክልሉ ችግኝ ጣቢያዎችን በመገንባትና መሰረተ ልማት በሟሟላት ለወጣቶች እየተሰጠ ሲሆን የወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትና የሥራ ዕድል ፈጠራም ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ እንደሆነ አመልክተዋል። በግብርና ሚኒስቴር የሆርቲካልቸር ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብደላ ነጋሽ በበኩላቸው የፍራፍሬ ምርቶች ላይ መስራት ለኢንዱስትሪው ግብዓት ምርት ለማግኘት እንደሚያግዝ ጠቅሰዋል።   በተጨማሪም የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ ፋይዳው የጎላ መሆኑንም እንዲሁ። ከዚህ አኳያም አቮካዶን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያላቸው የፍራፍሬ ችግኞችን መትከል አገራዊ ጠቀሜታቸው ከፍ ያለ መሆኑን ተናግረዋል። በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ ከተሳተፉት ሰራተኞች መካከል ወጣት እንኮይ ምትኩ የአገሪቷን ኢኮኖሚ ለማሳደግ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ፋይዳው ትልቅ ነው ብላለች። ሌላዋ የኢኒስቲትዩቱ ሰራተኛ ወጣት ሠናይት ግርማ በበኩሏ ችግኝ ከመትከል ባለፈ እንክብካቤ በማድረግ ለውጤት እንዲበቃ ማድረግ ከኛ ይጠበቃል ስትል ትናግራለች።      
አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ከመትከል ባለፈ የሀገር ሰላም፣ ልማት እና የብልጽግና ጉዞን የምናረጋግጥበት ነው - አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር
Jul 19, 2024 164
አርባ ምንጭ ፤ ሐምሌ 12/2016 (ኢዜአ)፡- የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ችግኝ ከመትከል ባለፈ የሀገር ሰላም፣ ልማት እና የብልጽግና ጉዞን የምናረጋግጥበት ነው ሲሉ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ። አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እና የጋሞ ዞን ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች በአርባ ምንጭ ዓሣ ጫጩት ብዜት ማዕከል ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል።   በመርሀግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር አረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ችግኝ ከመትከል ባለፈ የአገር ሰላምና ልማት የሚረጋገጥበት መሆኑን ተናግረዋል። ዘንድሮም መርህግብሩ "የምትተክል ሀገር የሚያጸና ትውልድ" በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፣ መርሀግብሩ የአገርን ሰላም፣ ልማትና የብልጽግና ጉዞን እውን የምናደርግበት ነው ብለዋል።   ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያስጀመሩት የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ የአገር ክብር የሚመልስ ተግባር ነው ሲሉም ገልጸዋል። ባለፉት አምስት ዓመታት 32 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ መተከሉን ያስታወሱት አቶ አገኘሁ፣ በእዚህም 20 በመቶ የነበረውን የአገሪቱ የደን ሽፋን ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ማደጉን ገልጸዋል። በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል እንደአገር ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል። የዘንድሮው መርሃ ግብር ችግኝ የሚተከልበት ብቻ ሳይሆን ሰላም፣ አብሮነት፣ አንድነትና ወንድማማችነትን በጽኑ መሠረት ላይ የምናቆምበት ጭምር ነውም ብለዋል። ህዝቡ በችግኝ ተከላው የነቃ ተሳትፎ ከማድረግ ባለፈ ልዩነቶችን ተቀራርቦ በውይይት ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶች እንዲሳኩ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል። የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አለማየሁ ባውዲ በበኩላቸው በክልሉ በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ መሆናቸውን ገልጸዋል።   ልማቱ ስኬታማ እንዲሆን በሁሉም የክልሉ ዞኖች የተራራ ልማት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንና ተስፋ ሰጪ ውጤት እየታየ መምጣቱንም ጠቅሰዋል። ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን የተተከለውን ችግኝ የመንከባከብ ተግባር የሁላችንም ሊሆን ይገባል ሲሉም ገልጸዋል። መንግስት ከወትሮው በተለየ መልኩ ለአረንጓዴ አሻራ ልማት ልዩ ትኩረት በመስጠቱ በዞናችን በስነ ምህዳርና በብዝሃ ህይወት ተጨባጭ ለውጥ ተመዝግቧል ያሉት ደግሞ የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባይነህ አበራ ናቸው።   በዚህም ባለፉት አምስት ዓመታት በ61 ሺህ 179 ሄክታር መሬት ላይ የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መተከላቸውን ነው የገለጹት። ዘንድሮም ችግኝ ከመትከል ባለፈ የጋራ እሴቶችን በማጠንከር ለመጪው ትውልድ የተሻለ አካባቢ ለመፍጠር በልዩ ትኩረት ይሰራል ብለዋል። በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፀሐይ ወራሳ፣ የብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አዳማ ቲምጳዬ እና የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገብረመስቀል ጫላ ተሳትፈዋል። በተጨማሪም ሌሎች የፌዴራል፣ የክልሉ፣ የዞንና የወረዳ ሥራ ኃላፊዎችና የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
በሲዳማ ክልል ጭስ አልባ ትራንስፖርትን ለማስፋፋት ስራዎች ተጀምረዋል-- የክልሉ መንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ
Jul 19, 2024 291
ሀዋሳ ፤ ሐምሌ 12/2016(ኢዜአ)፡- የሲዳማ ክልል ጭስ አልባ ትራንስፖርትን በማስፋፋት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚን የመገንባት ሂደቱን ውጤታማ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የክልሉ መንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ፡፡ ቢሮው የጭስ አልባ ተሸከርካሪዎችን የማስተዋወቂያ መድረክ በሃዋሳ ከተማ ትናንት አካሄዷል።   የክልሉ መንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ታምሩ ታፌ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ፖሊሲ ተፈጻሚነት የትራንስፖርት ዘርፉ ከፍተኛ ድርሻ አለው፡፡ በዚህም የሲዳማ ክልል እንደ አገር የተቀመጠውን ጭስ አልባ ትራንስፖርትን የማስፋፋት ተልእኮ በመቀበልና ፈጥኖ ወደ ስራ በመግባት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው ብለዋል፡፡ በዘርፉ ከተሰማሩ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ለሁለተኛ ጊዜ ጭስ አልባ ተሸርካሪዎችን የማስተዋወቅ ስራ ተሰርቷል ነው ያሉት፡፡ የጭስ አልባ ትራንስፖርት ከአረንጓዴ ልማት ጋር በእጅጉ የተቆራኘና ለህብረተሰቡ ምቹ አማራጭን ይዞ የመጣ በመሆኑ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታውን ማስተዋወቅና መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ ክልሉ በዘርፉ ከተሰማሩ ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው የትራንስፖርት አማራጩ ሰፊ የስራ እድል የሚፈጥር በመሆኑ ከባንኮች ጋር የማስተሳሰር ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም እንደ ሃገር ለተቀመጠው ፖሊሲና አቅጣጫ ተፈጻሚነት የትራንስፖርት ዘርፉ ሚና ከፍተኛ በመሆኑ የተጀመረውን ስራ ለማጠናከር የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ ስራ በትኩረት ይሰራል ብለዋል። በመድረኩ ከሲዳማ ክልል ከተለያዩ ዞኖችና ከሃዋሳ ከተማ የሚመለከታቸው የመንግስት ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት አመራርና ሠራተኞች የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር አካሄዱ
Jul 19, 2024 140
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 12/2016(ኢዜአ)፦ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት አመራርና ሠራተኞች በአዲስ አበባ ለሚኩራ ክፍለ ከተማ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር አካሄዱ። የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፤ የተቋሙ አመራሮችና ሠራተኞች በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በንቃት እየተሳተፉ ነው። የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የአየር ንብረት ለወጥ የሚያደርሰውን አሉታዊ ተፅዕኖ ከመከላከሉ ባሻገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን ነው ያስረዱት። መርኃ ግብሩ ከተረጅነት የሚያላቅቅ መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም ዜጋ ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ የሚያደርገውን አስተዋጽዖ ሊያጠናክር እንደሚገባም ተናግረዋል። በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር "የምትተክል ሀገር የሚያፀና ትውልድ" በሚል መሪ ሃሳብ 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ ነው።  
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአገር በቀል እጽዋቶችን መሰረት ያደረገ የአካባቢ ጥበቃ ስራ ለማከናወን ምቹ እድል ፈጥሯል
Jul 19, 2024 103
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 12/2016(ኢዜአ):- የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአገር በቀል እጽዋቶችን መሰረት ያደረገ የአካባቢ ጥበቃ ስራ ለማከናወን ምቹ እድል መፍጠሩን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምጸኃይ ጳውሎስ ተናገሩ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች ጋር በመሆን በጫካ ፕሮጀክት ሀገር በቀል የአረንጓዴ ዓሻራ ችግኞችን ተክለዋል። በመርሃ ግብሩም በባህር ዛፍ ተክል የተሸፈኑ ስፍራዎችን በአገር በቀል እጽዋቶች የመተካተ ስራ ተከናውኗል፡፡   የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምጸኃይ ጳውሎስ፤ የጽህፈት ቤቱ ሰራተኞች በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለሁለተኛ ጊዜ የሀገር በቀል ችግኝ ተከላ ማከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡ የጽህፈት ቤቱ ሰራተኞች ከዚህ ቀደም በአገር በቀል የእርከን ጥበብ በተዘጋጁ ቦታዎች ላይ የፍራፍሬ ችግኞችን መትከላቸውን አስታውሰዋል፡፡ በዛሬው እለት ደግሞ ቀደም ብለው በባህር ዛፍ ተሸፍነው በነበሩ ቦታዎ ላይ በሀገር በቀል ችግኞችችግኞች መትከላቸውን ጠቅሰዋል፡፡ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአገር በቀል እጽዋቶችን መሰረት ያደረገ የአካባቢ ጥበቃ ስራ ለማከናወን ምቹ እድል መፍጠሩንም ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ያለ ልዩነት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተሳትፎ በማድረግ ውጤታማ ስራ ማከናወናቸውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡ ይህ የጋራ ትብብር በዘንድሮው ዓመትም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በመርሃ ግብሩ የተሳተፉ የጽህፈት ቤቱ ሰራተኞች በበኩላቸው፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከአካባቢ ጥበቃ ባሻገር ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡ በጽህፈት ቤቱ የስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ጽጌ ብርሃኑ፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አካባቢን ከመጠበቅ ባሻገር በምግብ ራስን የመቻል ስራ አካል መሆኑን ተናግረዋል፡፡   ሌላኛው የጽህፈት ቤቱ ሰራተኛ አቶ ሙሉነህ ንጉሴ፤ አረንጓዴ አሻራ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በባለቤትነት የሚሳተፉበት መርሃ ግብር መሆኑን ተናግረዋል፡፡   መርሃ ግብሩ የተሻለች ሀገርን ለትውልድ ለማስተላለፍ እንደሚያስችል ጠቅሰው፤ ይህም የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡      
በዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለፍራፍሬ ልማትና አገር በቀል እጽዋት ትኩረት በመስጠት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው
Jul 19, 2024 103
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 12/2016(ኢዜአ)፦በዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለፍራፍሬ ልማትና ሀገር በቀል እጽዋት ትኩረት በመስጠት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች ጋር በመሆን በጫካ ፕሮጀክት ሀገር በቀል የአረንጓዴ አሻራ ችግኞችን ተክለዋል።   በመርሃ ግብሩም በባህር ዛፍ ተክል የተሸፈኑ ስፍራዎችን በአገር በቀል እጽዋቶች የመተካት ስራ ተከናውኗል፡፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ጊዜ፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተጀመረ ወዲህ በኢትዮጵያ ያለው የደን ሽፋን መሻሻል ማሳየቱን አንስተዋል፡፡ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአገር አቀፍ ደረጃ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን የመትከል እቅድ ተይዞ ወደ ስራ መገባቱንም ነው ያብራሩት፡፡ በመርሃ-ግብሩም ለፍራፍሬ ልማትና አገር በቀል እጽዋት ትኩረት በመስጠት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአካባቢ መራቆትን ከመከላከል ባሻገር ለግብርና ምርታማነትና ቱሪዝም ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለውም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡ በተለይ የአፈርና ውሃ ጥበቃን በማጎልበት ስንዴን ጨምሮ እንደ ሀገር የተያዙ የግብርና ኢኒሼቲቮችን ውጤታማ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል፡፡ እንደ ባህር ዛፍ ያሉና ከፍተኛ ውሃ የሚጠቀሙ ተክሎችን በሀገር በቀል እጽዋት መተካትም በመርሃ ግብሩ ትኩረት የተሰጠው ስራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ይህም በተለይ ከኢትዮጵያ አየር ጠባይ ጋር በተስማማ መልኩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራን ውጤታማ ለማድረግ እንደሚያግዝም ገልጸዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች በዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለሁለተኛ ጊዜ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ማከናወናቸውም ነው የተገለጸው፡፡    
የትምህርት ማህበረሰቡ በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የሚያደርገውን ተሳትፎ አጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል- ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር)
Jul 19, 2024 73
የትምህርት ማህበረሰብ በአገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ግቡን እሲኪመታ ተሳትፎቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ። የ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎችና ፈተና አስፈፃሚዎች የአረንጓዴ አሻራ የማኖር መርኃ ግብር በእንጦጦ ፓርክ አካሄዱ።   በመርኃ ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር)፣ በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት አመራሮች፣ የ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና የወሰድ ተማሪዎች፣ ፈተና አስፈፃሚዎችና መምህራን ተሳትፈዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ የትምህርቱ ማህረሰብ በሀገር አቀፍ ሆነ በከተማ ደረጃ በሚካሄዱ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በንቃት እየተሳተፈ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮም ባለፈው ሳምንት 30ሺህ መትከላቸውን ተናግረዋል። ዛፍ መትከልና አካባቢን መጠበቅ የትውልድ አደራ እንደሆነ ተናግረው፤ ትውልዱ ከአባቶቹ የተረከበውን ሀገር የማፅናትና የማስቀጠል ሃላፊነት ሊወጣ ይገባል። በዚህም መምህራን፣ ተማሪዎችና አጠቃላይ የትምህርት ማህበረሰብ በአገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ያለውን የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ግቡን እስኪመታ ተሳትፎቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል። የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች መልካም ውጤት እንዲገጥማቸው የቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) ተመኝተዋል። በችግኝ ተከላው የተሳተፉ የፈተና አስፈፃሚዎች ችግኞችን ከመትከል ባሻገር እንዲፀድቁ በየጊዜ ክትትል እና እንክብካቤ ማድረግ እንደሚገባቸው ተናግረዋል። የ2016 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር “የምትተክል ሀገር፣ የሚያፀና ትውልድ” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሔደ መሆኑ ይታወቃል። በመርኃ ግብሩም 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ ነው።  
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና ሠራተኞች አረንጓዴ አሻራቸውን አኖሩ   
Jul 19, 2024 125
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 12/2016(ኢዜአ):- የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና ሠራተኞች ዛሬ በአዲስ አበባ አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል። በችግኝ ተከላ መርኃ ግብሩ የምክር ቤቱ አመራሮች፣ የምክር ቤት አባላትና የጽህፈት ቤቱ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ተገኝተዋል። የምክር ቤቱ ምክትል አፈ-ጉባዔ ሎሚ በዶ በዚሁ ጊዜ፤ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብሩ እየተመናመነ የመጣውን የደን ሽፋን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው። በተጨማሪም ለአየር ንብረት ተጽዕኖ የማይበገር እንዲሁም ዘላቂነት ያለውን አገራዊ ልማት ለማረጋገጥ ከፍተኛ አዎንታዊ አስተዋጽዖ እንዳለው አስረድተዋል።   ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ተሳትፎቸውን እንዲያጠናክሩና የተተከሉት ችግኞች በመንከባከብ የዜግነት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል። የሕዝቡ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የአረንጓዴ አሻራ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ የነቃ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ገልጸው በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።   በዛሬው ዕለትም ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ ለማድረግ የሚያስችል ሥፍራ ከአራዳ ክፍለ ከተማ በመረከብ አረንጓዴ አሻራቸውን እንዳኖሩ ተናግረዋል። የተተኩሉት ችግኞች ለምግብነትና ለከተማ ውብት የሚያገለግሉ መሆናቸው ጠቅሰዋል በቀጣይ ችግኞቹን የመንከባከብና የመጠበቅ ሥራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።          
የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎችና ፈተና አስፈፃሚዎች የአረንጓዴ አሻራ መርኃግብር አካሄዱ
Jul 19, 2024 105
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 12/2016(ኢዜአ)፦ የ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎችና ፈተና አስፈፃሚዎች የአረንጓዴ አሻራ የማኖር መርኃግብር በእንጦጦ ፓርክ አካሄዱ። በመርሀ ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ሀላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር)፣ በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት አመራሮች፣ የ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች፣ ፈተና አስፈፃሚዎችና መምህራን ተሳትፈዋል።   የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) አንዳሉት ፤ የትምህርቱ ማህረሰብ በሀገር አቀፍ ሆነ በከተማ ደረጃ በሚካሄዱ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በንቃት እየተሳተፈ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮም ባለፈው ሳምንት 30ሺህ መትከሉን ተናግረዋል። መምህራን ተማሪዎችና ባለድርሻ አካላት በአገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ያለውን የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ግቡን እሲኪመታ ተሳትፎቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል። የትምህርት ቢሮ ኃላፊው ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች መልካም ውጤት እንዲገጥማቸው ተመኝተዋል። “የምትተክል ሀገር፣ የሚያፀና ትውልድ” በሚል መሪ ሀሳብ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እየተካሔደ መሆኑ ይታወቃል። በዘንድሮው ዓመት በሚካሔደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም