በሲዳማ ክልል የአረንጓዴ አሻራ ልማት የአየር ንብረት ለውጥን ከመጠበቅ ባለፈ ምርታማነትን እያሳደገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል የአረንጓዴ አሻራ ልማት የአየር ንብረት ለውጥን ከመጠበቅ ባለፈ ምርታማነትን እያሳደገ ነው

ሀዋሳ፤ ሰኔ 23/2017 (ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር የተከናወኑ የልማት ሥራዎች የአየር ንብረት ለውጥን ከመጠበቅ ባለፈ ምርታማነትን ማሳደጋቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ደስታ ዛሬ በዳራ ኦቲልቾ ወረዳ ሾይቾ ቀበሌ ተገኝተው የክልሉን የዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር አስጀምረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንደገለጹት በክልሉ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ሥራዎች የአየር ንብረት ለውጥን በመጠበቅና የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን አስገኝተዋል።
ዛሬ በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር የሚተከሉ ችግኞች ለመጪው ትውልድ የሚሻገሩ በመሆኑ ከመትከል ባለፈ በአግባቡ ጸድቀው እንዲያድጉ መንከባከብ ይገባል ብለዋል።
ዛሬ ክልል አቀፉ ተከላ የተጀመረበት ቦታ ከዚህ ቀደም የተራቆተ እንደነበረና በተደጋጋሚ በተሰራው የአረንጓዴ ልማት ሥራ ውጤት የተመዘገበበት በመሆኑ ወደሌሎች አካባቢዎችም ማስፋት ይገባል ብለዋል።
በክልሉ በክረምት ወራት የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች ለመትከል ዝግጅት መደረጉን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ የክልሉ ህዝብ በልማት ሥራው በተደራጀ መንገድ እንዲሳተፍም ጥሪ አቅርበዋል።
በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ፣ የክልሉ መንግስት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።